ቀጥታ፡

የገናሌ ዳዋ ቁጥር 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ውሃ መያዝ ጀመረ

ጎባ የካቲት 28 / 2011 የገናሌ ዳዋ ቁጥር 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት እየተጠናቀቀ መምጣቱን ተከትሎ ውሃ መያዝ መጀመሩ ተጠቆመ፡፡

የፕሮጀክቱ የልማት ተነሺዎች በበኩላቸው የካሳ ክፍያው ዘግይቶ ቢከፈላቸውም የፕሮጀክቱን ጠቀሜታ በመረዳት ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት ከፕሮጀክቱ አካባቢ በልማት ምክንያት ለሚነሱ ወገኖች የሚከፈል የካሳ ክፍያ መዘግየቱ ግድቡ ውሃ መያዝ ከነበረበት ጊዜ እንዲዘገይ አድርጓል፡፡

በአሁኑ ወቅት በፕሮጀክቱ ላይ የነበሩ ችግሮች ተፈተው ግድቡ ውሃ መያዝ መጀመሩን የገለጹት ዳይሬክተሩ እንደ ወንዙ የፍሰት መጠን ግድቡ ከስድስት ወር በኋላ ኃይል ወደማመንጨት ተግባር ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ግድቡ 2 ነጥብ 57 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 97 ነጥብ 7 በመቶ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጉጂ እና ባሌ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ እየተገነባ የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ 254 ሜጋ ዋት ኃይል እንደሚያመነጭ ይጠበቃል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በፕሮጀክቱ ኃይል ከማመንጨት በተጨማሪ የአካባቢው ማህበረሰብ ተደራጅቶ በዓሣ እርባታ እና በቱሪዝም ዘርፍ በመሰማራት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የግድቡን የሲቪልና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች እያከናወነ የሚገኘው የቻይናው ሲጂጂሲ ኩባንያ ሲሆን የአሜሪካው ኤም.ደብሊው.ኤች ደግሞ የማማከር ሥራዎችን እየሰራ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ለግድቡ ግንባታ ከአካባቢያቸው ከተነሱ የልማት ተነሺዎች መካከል አቶ አህመድ ዩሱፍ እንደተናገሩት የካሳ ክፍያው ዘግይቶ ቢከፈላቸውም የፕሮጀክቱን ጠቀሜታ በመረዳታቸው ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል።

መንግስት የአካባቢውን የልማት ተነሺዎች በዓሣ እርባታና በሌሎች ተጓዳኝ ሥራዎች በማደራጀት ከፕሮጀክቱ በዘላቂነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ያስቀመጠው አቅጣጫ ህዝቡ በፕሮጀክቱ ላይ አመኔታ እንዲኖረው የሚያድርግ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የልማት ተነሺ ሼህ ከድር አብዱራህማን ናቸው፡፡

ሁለቱ የልማት ተነሺዎች እንዳሉት መንግስት የከፈላቸው ፍትሃዊ የካሳ ክፍያ ፕሮጀክቱን እንደ ግል ንብረታቸው እንዲንከባከቡና እንዲጠብቁ የባለቤትነት ስሜት ፈጥሮባቸዋል፡፡  

ግንባታው በ2003 ዓ.ም የተጀመረው ይህ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አጠቃላይ የፋይናንስ ወጪው 451 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው ከቻይናው አግዚም ባንክ በብድር መገኘቱ ታውቋል።

ቀሪው 40 በመቶ በአገር ውስጥ የፋይናንስ አቅም የሚሸፈን መሆኑም ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በዚሁ ፕሮጀክት ሳቢያ ከልማታቸው ለተነሱ ከ5 ሺ ለሚበልጡ ሰዎች 3 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የካሳ ክፍያ መፈጸሙን በቅርቡ ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም