በከተማዋ የተማሪዎች ሰርቪስ አገልግሎት እጥረት አሁንም እልባት አላገኘም-- የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
በከተማዋ የተማሪዎች ሰርቪስ አገልግሎት እጥረት አሁንም እልባት አላገኘም-- የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች

የካቲት 28/2011 በአዲስ አበባ የተማሪዎች ሰርቪስ አገልግሎት ከጀመረ ሁለት አመት ቢያስቆጥርም አሁንም ችግሩ እንዳልተቀረፈ ነው ያናገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የሚገልፁት።
ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ አውቶቢሶች በከተማዋ ዋና ዋና አደባባዮች ቢታዩም በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ከፍተኛ ክፍተት እንደሚታይበትም ነዋሪዎቹ ያነሳሉ።
በከተማዋ የዳግማዊ ምኒሊክ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርትና ወላጅ የሆኑት አስካላየሁ በቀለ እንደሚሉት በትምህርት ቤታቸው ከረጅም ርቀት ተጉዘው የሚመጡ በርካታ ተማሪዎች ሸገር የተማሪዎች ሰርቪስን ለመጠቀም ፍላጎቱ ቢኖራቸውም ቦታ የለንም በሚል አገልግሎቱን ሊጠቀሙ አልቻሉም።
ሁለት ልጆቻቸውን ከጣፎ ይዘው እንደሚመጡ የተናገሩት መምህርት አስካላየሁ “ሸገር አጠገቤ ቆሞ ሲጭን አያለሁ፤ በገንዘብም መሆኑን እረዳለሁ፤ ዋጋውም ከንግድ የተሻለ መሆኑን እረዳለሁ፤ ሆኖም አሰራሩ ላይ ተቋሙ ለግል ትምህርት ቤቶች ያደላ በመሆኑ ለመጠቀም ተቸግረናል” ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡
በቀን ከ40 ብር በላይ እያወጡ ልጆቻቸውን እያስተማሩ ያሉት መምህርቷ ሌሎች የትራንስፖርት ተቋማትም አገልግሎቱን በስፋት ሊጀምሩ ይገባል ይላሉ።
በዚሁ ትምህርት ቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ጌታሁን ጠገራው ትምህርት ቤቱ የአካቶ ትምህርት ከሚሰጥባቸው ጥቂት ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁሞ በርካታ ማየት የተሳናቸውና አካል ጉዳተኞች ከርቀት የሚመጡ ቢሆንም አንዳቸውም የዚህ የሰርቪስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳልሆኑና እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ግንዛቤው የሌለው መሆኑን ነው የነገረን፡፡
በዚህም የተነሳ ተማሪዎቹ በአንበሳ አውቶቢስ እየተጋፉ እንደሚሄዱና አብዛኛውን ግዜ እያረፈዱ እንደሚገቡ የነገረን ተማሪ ጌታሁን የሸገር ሰርቢስ ለመጠቀም እንዴት እንውደሆነ ግንዛቤው እንደሌለውና የተማሪዎች ሰርቪስ በትምህርት ቤታቸው በኩል ቢመቻች ከወጪና ከእንግልት እንድን ነበር ይላል፡፡
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የእድገት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት ያሰሚን ሽፋ በበኩላቸው በትምህርት ቤታቸው በርከት ያሉ ተማሪዎች የሸገር የተማሪዎች ሰርቪስ ተጠቃሚ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡
ከቡራዩ፣ ከአሸዋ ሜዳና ከሌሎች ሩቅ አካባቢዎች የሚመጡ ተማሪዎች የሰርቪሱ ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚገልጹት መምህርት ያሰሚን ካለው ፍላጎት አንጻር የሚሰጠው አገልግሎት ግን ዝቅተኛ ነው ይላሉ፡፡
በአካባቢው የአማርኛ ቋንቋ ትምርት ቤት ባለመኖሩ ከቡራዩ እድገት ትምህርት ቤት ለመማር በሸገር የተማሪዎች ሰርቪስ እንደሚሄድ የተናገረው የ8ኛ ክፍል ተማሪ እስክንድር ተፈሪ፤ ከዚህ በፊት ለሚኒባስ ይከፍል የነበረው ስድስት መቶ ብር በግማሽ ቀንሶ በተመቻቸ ሁኔታ ሰርቪሱን እየተጠቀመ መሆኑን ይናገራል።
ባለፉት ዓመታት ትምህርቱን ሲከታተል በአንድ ሚኒባስ ከ20 በላይ ተማሪዎች ታጭቀው ይጉዋዙ እንደነበርም ነው ተማሪ እስክንድር ያስታወሰው።
ካለፈው ዓመት ጀምሮ የተማሪዎች ሰርቪስ የሚል አውቶቢስ በግል ትምህርት ቤቶች ደጃፍ ላይ ከመታየቱ ውጭ ስለአጠቃቀሙ ምንም ግንዛቤ የሌላቸው በመሆኑና በመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ አገልግሎቱ በስፋት እንደማይታይ የተናገሩት ደግሞ የዳግማዊ ምኒሊክ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር አለማየሁ ነጋሽ ናቸው፡፡
“ይህ የሆነበት ሁኔታ ግልጽ አይደለም” ያሉት መምህር አለማየሁ በተለይ ትምህርት ቤታቸው የአካቶ ትምርት መስጫ ማዕከል እንደመሆኑ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ስለሚማሩበት ትኩረት ሊያገኝ ይገባ ነበር ይላሉ፡፡
የሸገር ብዙሃን ትራንስፖርት የኮሙኒኬሽን ስራ ሂደት ሃላፊ አቶ ሳሙኤል ፍሰሃ ስለ ሁኔታው ተጠይቀው የህብረተሰቡ ቅሬታ ትክክል ነው ይላሉ።
ሸገር ባለፈው ዓመት በሰላሳ አውቶቢሶች በሰባት መስመሮች የጀመረውን አገልግሎት ዘንድሮ ቁጥሩን በማሳደግ 100 አውቶቢሶችን ቢያሰማራም አሁንም አገልግሎቱን በተሟላ መልኩ ማዳረስ እንዳልቻለም ይገልጻሉ።
በከተማዋ የአገልግሎት ፈላጊ ተማሪ ቁጥርና እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ሊመጣጠን እንዳልቻለ የተናገሩት አቶ ሳሙኤል በአሁኑ ወቅት በ75 መስመሮች ላይ ስምሪት በማድረግ ሶስት ሺህ ሶስት መቶ ተማሪዎችን ብቻ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
ሸገር ለመንግስትም ሆነ ለግል ትምህርት ቤቶች አገልግሎቱን እንደሚሰጥ የተናገሩት አቶ ሳሙዔል ክፍያው እንደ ኪሎ ሜትሩ ርቀት በወር ከ250 አስከ 600 ብር የሚያስከፍል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ለህብረተሰቡ በትምህርት ቤቶች በኩል ግንዛቤ እንዲፈጠር መደረጉንና በቂ መኪኖች ሲሰማሩ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስና አገልግሎቱን ለማስፋት በቀጣይ ዓመት ተጨማሪ አውቶቢሶችን ለማሰማራት ጥናት አድርጎ ለሚመለከተው የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ማሳወቁንም አብራርተዋል፡፡