ቀጥታ፡

በአርባምንጭ ተደራጅተው የገንዘብ ድጋፍ የሚጠብቁት ወጣቶች ወደ ስራ መግባት እንዳልቻሉ ገለጹ

አርባ ምንጭ የካቲት 27/2011 በግንባታው ዘርፍ ለመሰማራት በማህበር ተደራጅተው ከመንግስት የሚጠብቁት የገንዘብ ድጋፍ በመዘግየቱ ወደ ስራ መግባት እንዳልቻሉ በአርባምንጭ ከተማ የሚገኙ ወጣቶች ገለጹ፡፡

በአርባ ምንጭ የነጭሳር ክፍለ ከተማ ነዋሪው ወጣት ዘርሁን ፍቃዱ እንዳለው በግንባታው መስክ ለመሰማራት አስር ሆነው የተደራጁት በ2011 የበጀት ዓመት ነሐሴ ወር ውስጥ ነው፡፡

ተደራጅተው የሚጠበቅባቸውን በማጠናቀቅ ስራ ለመጀመር የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ በመንግስት በኩል በመዘግየቱ እየተጉላሉ መሆናቸውን ተናግራል፡፡

"ይህም በጊዜ ወደ ሥራ ገብተን እንዳንለወጥ ከማድረጉም በላይ ቅሬታ ውስጥ ከቶናል፤የበጋ ወራትን ሳንጠቀም ክረምት እየመጣ ነው " ብሏል፡፡

ከማህበራት አደረጃጀት ጋር በተያያዘ መንግስት የጀመረውን የማጣራት ሥራ በማፋጠን በጨረታ ያሸነፉትን ስራ እንዲያከናውኑ ገንዘቡ ፈጥኖ እንደሚቻችላቸው ጠይቋል፡፡

የድል በትግል ጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ማህበር አስተባባሪ ወጣት ትዕግስት ዓባይነህ በበኩሏ ማህበሩ ከተቋቋመበት ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ ሁለት  የግንባታ ፕሮጀክቶችን  በጥራት መሥራታቸውን ተናግራለች፡፡

በዚህ ስራ ወቅት ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ ችግር እንዳላጋጠማቸው አስታውሳ ዘንደሮ ግን ሌላ ግንባታ ላይ ለመሰማራት ክፍያ የማስፈጸሙ ሂደት መዘግየቱን ገልጻለች፡፡

ባለሀብቶችና የመንግስት ሠራተኞች በወጣቶች የሥራ ዕድል እየተሻሙ መሆናቸውን ተከትሎ መንግስት የጀመረውን የማጣራት ሥራ በአፋጣኝ ማጠናቀቅ እንደሚገባም አመልክታለች፡፡

በተመሳሳይ በድንጋይ ንጣፍ መንገድ ስራ ለመሰማራት ከሌሎች ወጣቶች ጋር በማህበር እንደተደራጀ የተናገረው የሲቀላ ክፍለ ከተማ ነዋሪ  በዛብህ መለሰ በበኩሉ መንግስት ወጣቱን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ የሰጠው ትኩረት እንደሚደግፍ ገልጿል፡፡

ሆኖም በበጀት ዓመቱ ተደራጅተው ወደ ስራ ለመግባት በአርባ ምንጭ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በኩል በአግባቡ መስተናገድ ባለመቻላቸው ለአምስት  ወራት ያህል መጉላላታቸውን ተናግሯል፡፡

በየጊዜው ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ስራ መጀመር የሚያስችላቸውን ገንዘብ እንዳላገኙና ስራቸውን በወቅቱ ማካሄድ  እንዳልቻሉ ገልጿል፡፡

የሚመለከተው የመንግስት አካልም ችግራቸውን በመረዳት ወደ ስራ መግባት እንዲችሉ ድጋፉ እንዲፋጠንላቸው ጠይቀዋል፡፡

በአርባ ምንጭ አስተዳደር  ማዘጋጃ ቤት ሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኢያሱ አላሮ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ "በግንባታው  ዘርፍ መሠረታዊ የአደረጃጀት ችግሮች በመኖራቸው እያጣራን ነው" ብለዋል ፡፡

በዘርፉ ብዛት ያላቸው  ባለሀብቶችና የመንግስት ሠራተኞች በሥራ አጥ ስም እየተደራጁ በመሆኑ ይህም  ቅሬታ ማስነሳቱንም ተናግረዋል፡፡

"ባለፉት ስድስት ወራት በግንባታው ዘርፍ በተደራጁ 92 ማህበራት ላይ በተደረገው የማጣራት ሥራ በ30 ማህበራት ላይ ጉድለት መኖሩን ደርሰንበታል" ብለዋል ፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የድጋፍ አግባቦች በተዋጣ መልክ እንዳይሰጥ እንቅፋት መሆኑን ጠቅሰው አዳዲስ ማህበራትም በጥንቃቄ ሊደራጁ እንደሚገባ አሳስበዋል ፡፡

የክፍያ ስርዓቱ ከዚህ በኋላ እንደሚፋጠንም አቶ ኢያሱ ጠቁመዋል ፡፡

በግማሽ የበጀት ዓመቱ ከ2ሺህ በላይ ወጣቶች በዚሁ ዘርፍ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሆኑ አመልክተው ከመካከላቸውም 847 ሴቶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም