ቀጥታ፡

9ኛው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ኤግዚቢሽን ተጀመረ

አዲስ አበባ የካቲት 27/2011የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የቴክኖሎጂ ዕድገት ቀጣይነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ብቁ የሰው ኃይል የማፍራትና የኢንተርፕራይዞች አቅም የመገንባት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገለጸ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተዘጋጀውና ዛሬ የተጀመረው 9 ኛው የቴክኒክና ሙያ ኤግዚቢሽን እስከ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል።

በኤግዚቢሽኑ መክፈቻ ላይ የከተማዋ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው እንዳሉት አስተዳደሩ በቴክኒክና ሙያ የሰለጠነ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት እየተሰራ ነው።

ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች ችግር ፈቺ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በመቅዳትና ለኢንተርፕራይዞች በማሸጋገር የኢንዱስትሪ አንቀሳቃሽ ሞተር እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የቴክኖሎጂ ዕድገት ቀጣይነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ብቁ የሰው ኃይል የማፍራትና የኢንተርፕራይዞች አቅም ለመገንባት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው።

በዝግጅቱ ላይ የተለያዩ ፈጠራዎችን ያቀረቡት ተማሪዎች እንዳሉት፤ የኤግዚቢሽኑ መዘጋጀት ያመረቱትን ምርት ለማስተዋወቅና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማከናወን ያግዛል ።

"ለኢንዱስትሪ ዕድገታችን ቴክኒክና ሙያ የመጀመሪያ ምርጫችን" በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን ላይ በከተማዋ የሚገኙ 115  የመንግስት የግል ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማትና 600 የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ የሚደርግላቸው ሞዴል ኢንተርፕራይዞች ተሳታፊ ናቸው።

በኤግዚቢሽኑ ላይ በተቋማቱ የተሰሩ ከ1 ሺህ በላይ አዋጭና ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለዕይታ ቀርቧል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ በመንግስትና በግል ከ42 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰልጠኞች በመደበኛ መርሃ ግብር እየተማሩ ሲሆን በኢንዱሰትሪ ኤክስቴንሽን ከ10 ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞች አሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም