የ20/80 እና የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ወጣ - ኢዜአ አማርኛ
የ20/80 እና የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ወጣ

አዲስ አበባ የካቲት 27/2011 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያስገነባቸውን 51 ሺህ 229 የ20/80 እና የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ በማውጣት ለእድለኞች ይፋ አደረገ።
የ13ኛ ዙር የ20/80 እና የ2ኛ ዙር የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት ዛሬ በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ተካሂዷል።
በእጣው የ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም 1 ሺህ 248 ስቲዲዮ፣18 ሺህ 823 ባለ አንድ መኝታ፣ 7 ሺህ 127 ባለ ሁለት መኝታና 5 ሺህ 455 ቤቶች ደግሞ ባለ3 መኝታ መሆናቸው ታውቋል።
በእጣ አወጣጡ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በታዛቢነት የተጋበዙ የታደሙ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
በዕጣው የተካተቱት በ1997ዓ.ም ምዝገባ አካሂደው በ2005 ዓ.ም በነባር መደብ የተመዘገቡና በ2005 ዓ.ም የአዲስ ባለ3 መኝታ ተመዝጋቢዎች መሆናቸው ታውቋል።
ሌላኛው መስፈርት በነባር መደብ ተመዝግበው 40 ተከታታይ ወራትን የቆጠቡና የባለ3 መኝታ አዲስ ተመዝጋቢዎች ደግሞ ለ60 ተከታታይ ወራት የቆጠቡ መሆኑም ተገልጿል።
እጣው 5 በመቶ አካል ጉዳተኞችን 30 በመቶ ሴቶችንና 20 በመቶ የመንግስት ሰራተኞችን ተጠቃሚ ማድረጉም ታውቋል።
በሁለተኛው ዙር በ40/60 ለእጣ ከቀረቡ 18 ሺህ 576 ቤቶች 3 ሺህ 60 ባለ 1 መኝታ፣10 ሺህ 322 ባለ 2 መኝታና 5 ሺህ 194 ባለ 3 መኝታ መሆናቸው ተገልጿል።
በእነዚህ የቤቶች እጣ ወስጥ ለመግባትም ተመዝጋቢዎች በመጀመሪያው ምዝገባ ወቅት ከነበረው ጠቅላላ ዋጋ ቢያንስ 40 በመቶ የቆጠቡ መሆናቸው ተጠቁሟል።
ለባለ 1 መኝታ 65 ሺህ 58 ብር ፣ለባለ2 መኝታ 100 ሺህ ብር፣ለባለ 3 መኝታ ደግሞ 154 ሺህ 560 ብር የቆጠቡ ናቸው።
በ40/60 የቤቶች ልማት ፕሮግራም ለመንግስት ሰራተኞች 20 በመቶ ኮታ መሰጠቱም ተገልጿል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከ178,000 በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው በ12 የተለያዩ ዙሮች ለተመዝጋቢዎች በዕጣ መተላለፋቸው ይታወሳል።