ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ ቆጠራ ኮሚሽን አደረጃጀቶች በተጠናከረ መልኩ ወደ ስራ እንዲገቡ አሳሰቡ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ ቆጠራ ኮሚሽን አደረጃጀቶች በተጠናከረ መልኩ ወደ ስራ እንዲገቡ አሳሰቡ
አዲስ አበባ የካቲት 27/2011 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የህዝብ ቆጠራ ኮሚሽን አደረጃጀቶችን በተጠናከረ መልኩ ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚገባ አሳሰቡ።
የኮሚሽኑ አባላት ዛሬ ባካሄዱት አምስተኛ መደበኛ ስብሰባ የአራተኛውን የህዝብና ቤቶች ቆጠራ የዝግጅት ተግባራት አፈፃፀም በሚመለከት ውይይት አካሂደዋል።
የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የህዝብና ቤት ቆጠራ ሥራውን በተያዘለት ጊዜ ለማከናወን የሚያስችል አደረጃጀት ማቋቋም አስፈላጊ ነው።
ለቆጠራው የተደራጁ የቴክኒክ፣ የበጀት፣ የሰው ኃይል፣ የትምህርት ቅስቀሳ እና የሎጀስቲክ ትራንስፖርት ኮሚቴዎችን በሙሉ ኃይል ወደ ሥራ ማስገባት ይገባል ነው ያሉት።
መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም በይፋ የሚጀመረውን ቆጠራ የሚያስፈጽሙ አደረጃጀቶች በየደረጃው እንዲቋቋሙ መደረጉን አመልክተው፤ የማደራጀት ሥራው የዘገየባቸው አስተዳደሮች ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
የህዝብና ቤት ቆጠራ መረጃው ለሀገር ልማትና ዕድገት ካለው ፋይዳ አኳያ በሁሉም ዘንድ ተጠባቂ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ሆኖም በአንዳንድ ወገኖች የሚናፈሱት አሉታዊ ቅስቀሳዎች በቆጠራው ሂደትና ውጤት ላይ ችግር እንዳይፈጥር ከላይ እስከታች ያለው መዋቅር የተጠናከረ ትምህርትና ቅስቀሳ መስራት ይኖርበታልም ነው ያሉት።
በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ የሚስተዋሉ የፀጥታ ሥጋቶች ለህዝብና ቤቶች ቆጠራ ሥራው እክል እንዳይሆኑ የፀጥታ መዋቅሩ በተቀናጀ አግባብ በስኬት እንዲጠናቀቅ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅበት ገልፀዋል።
የክልል ተወካዮች በበኩላቸው በየአካባቢያቸው እያደረጉት ስላለው ዝግጅትና እያጋጠሟቸው ያሉ ችግሮችን በተመለከተ በውይይቱ ወቅት አንሰተዋል።
ለህዝብና ቤት ቆጠራው መረጃ የመሰብስብ ሥራ 180 ሺህ የሚደርሱ ታብሌቶች እና ፓወር ባንኮች መገዛታቸው የሚታወስ ሲሆን፤140 ሺህ 966 ቆጣሪዎች 38 ሺህ 162 ተቆጣጣሪዎች 1 ሺህ 173 የአይሲቲ አስተባባሪዎች ለቆጠራው ተዘጋጅተዋል።
በአጠቃላይ 180 ሺህ 302 የሚደርስ የሰው ኃይል ለዚሁ ተግባር እንደሚሰማራ ታውቋል።
ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራ መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም በመላ አገሪቱ ቆጠራው ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።