"ደራሽ" የተባለ አዲስ የክፍያ መተግበሪያ ቴክኖሎጂ ይፋ ሆነ

81

  አዲስ አበባ  የካቲት 27/2011 የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ "ደራሽ" የተባለ አዲስ አገር አቀፍ የክፍያ መተግበሪያ ቴክኖሎጂ ይፋ አደረገ።

አዲሱ ቴክኖሎጂ ግብር፣ ኪራይና ቅጣት መክፈል የሚያስችል ሲሆን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በቀላሉ ክፍያቸውን ለመሰብሰብና ለመከታተል የሚያስችላቸው እንደሆነ ተጠቁሟል።

ተጠቃሚው ህብረተሰብ በሚመቸው መንገድና በመረጠው ቦታ ሆኖ በፈለገው ተቋም አማካኝነት በመጠቀም የሚፈልገውን አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል አዲስ ቴክኖሎጂ መሆኑም ተገልጿል።

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የተቀናጀና የፕላን ፎርም ዲቪዥን ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ኃያሌው ቴክኖሎጂው ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደገለጹት "ደራሽ" በአገልግሎት ሰጪና በህብረተሰቡ እንዲሁም በፋይናንስ ተቋማትና መካከል ያለውን ግኑኙነት ቀላልና ቀልጣፋ ያደርጋል።

አገልግሎቱ ግብር ፤ኪራይና ቅጣት መክፈል የሚያስችል ሲሆን አገልግሎት ሰጪዎች በቀላሉ ክፍያቸውን ለመሰብሰብና ለመከታተል የሚያስችላቸው እንደሆነም አስረድተዋል።

በሞባይል ፤በኢንተርኔትና በባንኮች መክፈልና አገልግሎቱን መጠቀም የሚቻል ሲሆን አገልግሎት ሰጪውም ያለውን ሲስተም በማገናኘት መስራት ወይም ዳታዎች በማዘጋጀት በቅንጅት መስራት ይቻላል።

አገልግሎቱን ለማግኘት የሚከፈለው ክፍያ ተመጣጣኝና በጋራ በሚደረግ ውል መሰረት በመሆኑ ያለስፈላጊ ጭማሪ እንደማይደረግም ተናግረዋል።          

አገልግሎቱ ከመጀመሩ በፊት ለስምንት ወራት ያክል ከኢትዮጵያ ገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተመረጡ ግብር ከፋዮች ይህን ሥርዓት እንዲጠቀሙ በማድረግ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ታክስ ገቢ ማድረግ መቻሉንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የ"ደራሽ" ክፍያ መተግበሪያ ቴክኖሎጂ ያለ አግባብ የሚባክን ጊዜን በማስቀረት በአጭር ጊዜ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ዘመናዊ አሰራርን የሚከተል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም