የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የክለቦች የቼዝ ሻምፒዮና ዛሬ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የክለቦች የቼዝ ሻምፒዮና ዛሬ ተጀመረ
አዲስ አበባ ግንቦት 22/2010 በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቼዝ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ዛሬ በወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ተጀምሯል። በወንድ ፆታ እና በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በተወሰነው በዚህ ውድድር የሚሳተፉት ቡድኖች አቡጊዳ፣ አፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ፣ አዲስና ፔራት የተሰኙ የቼዝ ክለቦች ብቻ ናቸው። ክልሎች ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥያቄ ቢቀርብም በበጀት እጥረትና ክለቦቹ ባለመደራጀታቸው የተነሳ መሳተፍ እንዳልቻሉ የኢትዮጵያ የቼዝ ፌዴሬሽን አስታውቋል። በአሁኑ ወቅት ያሉት የቼዝ ስፖርት ክለቦች እጅግ አነስተኛ ቢሆኑም ፌዴሬሽኑ ግን በአራት ክለቦች የሻምፒዮና ውድድሩን ጀምሯል። የፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰፌ በላይነህ ለኢዜአ እንደተናገሩት የሻምፒዮናው ዓላማ በዘርፉ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራትና ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ማድረግ ነው። ከዚህም ሌላ ስፖርቱ በአገሪቷ እንዲስፋፋና እንዲጠናከር ከማድረግ አኳያም ውድድሩ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል። በመጪዎቹ አራት ቀናት በሚቆየው በዚህ ውድድር አሸናፊ ለሚሆኑ ክለቦች የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት ይበረከታል።