ሁሉም የመገጣጠምያ ህመሞች የዩሪክ አሲድ ክምችት ችግሮች አይደሉም -የህክምና ባለሙያ

የካቲት 27/2011 ዩሪክ አሲድ ከሚፈለገው በላይ በሰውነት ውስጥ ሲጠራቀም ለሪህ ህመም ምክንያት ቢሆንም ሁሉም የመገጣጠምያ ህመሞች ግን በዩሪክ አሲድ መብዛት እንደማይመጡ ይጠቀሳል፡፡

አቶ ብርሃኑ ወ/ዮሃንስ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለህክምና ክትትል የመጡ የሪህ ህመምተኛ አባት ናቸው፤መጀመሪያ ህመሙ የጀመራቸው ጉልበታቸው አካባቢ ቀጥሎም ወደ ቁርጭምጭሚት እያለ ወደ አውራጣታቸው በመዞር ከፍተኛ ህመም እንደሚፈጥርባቸው ነው የነገሩን፡፡  

ለህመማቸው ምክንያትም በወጣትነት ዕድሜያቸው አዘውትረው ሲመገቡት የነበረው ስጋ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸው ነግረውናል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ሽሮ ሲመገቡ ህመሙ እንደሚሰማቸውም ይገልጻሉ፡፡

’’በሆነ ወቅት መጥቶ ህመም ይፈጥራል፡፡ ድንገት ጥፍት ብሎ ከርሞ እንደገና ይመለሳል’’ ነው ያሉት፡፡

ከአዳማ የሪህ በሽታን ለመታከም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መጥተው ያገኘናቸው መምህር ካሳሁን በላይ ህመማቸውን ያወቁት በህክምና ምርመራ ነው፡፡ ህመሙ ሲነሳባቸው አውራ ጣታቸውን በመውጋት የህመም ስቃይ እንዳለውም ይናገራሉ፡፡

መምህር ካሳሁን ስጋ ተጠቃሚ እንደሆኑና ከስጋ በተጨማሪ የሚከለከሉ የምግብ ዓይነቶች ሲመገቡ በሽታው እንደሚጸናባቸው ይገልጻሉ፡፡

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ህክምና ትምህርት ክፍል ሃላፊና የኩላሊት ሃኪም  ዶ/ር አዲሱ መልኬ እንደሚሉት ዩሪክ አሲድ በሰዎችም ሆነ በእንስሳት በየጊዜው ያለማቋረጥ የሚመረት የሰውነት የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ውጤት ነው፡፡

የዩሪክ አሲድ መመረትና መወገድ ሂደት መዛባት መጠኑ በሰውነት ውስጥ በመጨመር መገጣጠምያ ላይ ወደ ጠጣር ነገሮች ተቀይሮ ቁስለትን በመፍጠር ጉዳት እንደሚያስከትል ነው ዶ/ር አዲሱ ያብራሩት፡፡

አንዳንዴ ጠጣር ነገሮቹ ከመገጣጠምያ አጥንት አልፈው የኩላሊት ጠጠር  እንደሚፈጥርም ነው ያነሱት፡፡

ዩሪክ አሲድ በሰውነት ውስጥ ከሚፈለገው በላይ ሲመረት ሪህ ለተባለ የመገጣጠምያ ህመም ተጋላጭ  ቢያደርግም ሁሉም የመገጣጠምያ ህመሞች ግን በዩሪክ አሲድ መብዛት እንደማይመጡ ዶ/ር አዲሱ ሙያዊ ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡

የዩሪክ አሲድ መጠን የሚበዛው በብዛት ተመርቶ በዛው ልክ ሳይወገድ ሲቀር እና በተፈጥሮ ዩሪክ አሲድ የማስወገድ አቅም አነስተኛ መሆን ዋነኞቹ ምክንያቶች  እንደሆኑም ነግረውናል፡፡

ከፍተኛ ውፍረት፣ ለሌሎች ህመሞች የሚወሰዱ መድሃኒቶችና የኩላሊት ህመም እንዲሁም የአመጋገብ ስርዓት ለዩሪክ አሲድ መብዛት አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር  አዲሱ የፕሮቲን ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦች አጋላጭ ቢሆኑም ሁሉም ግን አይጨምሩም  ይላሉ፡፡

የፕሮቲን ይዘት ኖሯቸው ዩሪክ አሲድ በከፍተኛ ደረጃ ከሚጨምሩ ምግቦች መካከል ቀይ ስጋ፣ የሆድ እቃ ስጋዎች(ጉበት፣ኩላሊትና ሌሎች)፣ ዓሳና የባህር ምግቦች  ተጠቃሽ እንደሆኑም ነው የተነገረው፡፡

የጥራጥሬ እህሎች እንደ አተር፣ ሽምብራ፣ ባቄላ፣ ምስርና የመሳሰሉት የፕሮቲን ይዘታቸው ከፍተኛ  ቢሆንም ዩሪክ አሲድ እንደሚጨምሩ ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ ማረጋገጫ እንደለሌም  ዶ/ር አዲሱ ይገልጻሉ፡፡

’’የሪህ ህመም የመመላለስ ባህሪ ሰላለው አንዳንድ ታማሚዎች እነዚህን የጥራጥሬ ውጤቶች ሲጠቀሙ እንደሚነሳባቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ፤ ይሄ ግን ትክክል አይደለም’’  ነው ያሉት፡፡

ወተትና የወተት ተዋጽኦ ከፍተኛ ፕሮቲን ቢኖራቸውም የዩሪክ አሲድ ክምችት ሊቀንሱ እንደሚችሉም  ባለሙያው አያይዘው ነግረውናል፡፡ 

የሪህ ህመም በወቅቱ ህክምና ካልተደረገለት የአካል ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ያሉት ዶ/ር አዲሱ በብዛት በአውራ ጣት ላይ ምልክት ቢያሳይም ጀርባ ፣ጉልበትና ሌሎች መገጣጠምያ አካላትን በማጣመም የአካል ጉዳት እንደሚያደርስም ይጠቅሳሉ፡፡

የሪህ ህመም መቆጣጠር እንጂ ፈጽሞ ማዳን አይቻልም  የሚሉት ዶክተር አዲሱ  ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ምልክቶቹ ባይታዩም በአመት ሁለት ጊዜ የጤና ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

ህመሙ ብዙን ጊዜ በወንዶች ላይ በ40ዎቹ የዕድሜ ክልል፤ በሴቶች ላይ ደግሞ ከ60 ዓመት በኋላ መታየት እንደሚጀምርም ነው የተገለጸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም