ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ በ4ኛው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ የዝግጅት ምዕራፍ ላይ እየመከረ ነው

አዲስ አበባ የካቲት 27/2011 የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ኮሚሽን አባላት 4ኛውን የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ሂደት በተመለከተ ዛሬ በአዲስ አበባ እየመከሩ ነው።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት እየተካሄደ ያለው ስብሰባ በቆጠራው የዝግጅት ምዕራፍ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ተነስተዋል።

የኮሚሽኑ አባላት የቆጠራ ሂደቱ በክልሎች ያለበትን ደረጃ የገመገሙ ሲሆን በአሁኑ ወቅት እያጋጠሙ ላሉ ችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫ ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ የቆጠራ ሂደቱ አንዳንድ ችግሮች እያጋጠሙት መሆኑን ገልጸዋል።

የአስተዳደርና ወሰን ጉዳይ፣ የብሔረሰብና የማንነት ጉዳይ፣ የስልጠና ቦታ አለማግኘት፣ የተቆጣጣሪና የቆጣሪዎች ምልመላ ጥራት ማነስ፣ የቆጠራ ኮሚሽን ኮሚቴ በወረዳዎችና በቀበሌዎች ደረጃ አለመዋቀር፣ አሉታዊ ቅስቀሳ መስፋፋት ያጋጠሙ ችግሮች እንደሆኑ አመልክተዋል። 

እንዲሁም በተወሰኑ ቦታዎች የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች መፍትሄ አለማግኘት እያጋጠመ ያለ ፈተና መሆኑን ገልጸዋል።

የቆጠራ ቦታ ካርታ ያልተሰራላቸው አካባቢዎች ካርታ እንዲሰራላቸው ማድረግ፣ የቆጠራ ኮሚሽን አደረጃጀቶችን በሙሉ ኃይል ወደ ስራ ማስገባት፣ የሰው ኃይል ምልመላና የስልጠና ማዕከላት ዝግጅት ማድረግ፣ የትምህርት ቁሳቁስ አደረጃጀቶችን ማጠናከርና የበጀት ጉድለት ላይ ማስተካከያ ማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ ከኮሚሽኑ እንዲሰጥ አቶ ቢራቱ ጠይቀዋል።

የሰው ኃይል ዝግጅትና ምልመላ፣ የቆጠራ ቴክኖሎጂ መሳሪያ (ታብሌት)፣ የህትመትና ሎጂስቲክስ ዝግጅትና ስልጠናዎች ማካሄድ እስከ አሁን ከተከናወኑ ተግባራት ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራ መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም በመላው አገሪቱ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም