ወላይታ ድቻ በሊጉ የሁለተኛ ዙር ውድድሮች የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እሰራለሁ አለ - ኢዜአ አማርኛ
ወላይታ ድቻ በሊጉ የሁለተኛ ዙር ውድድሮች የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እሰራለሁ አለ

ሶዶ የካቲት 27/2011 የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የ2011 ሁለተኛ ዙር ውድድሮች የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰራ አዲሱ ዋና አሰልጣኝ አስታወቁ፡፡
ለክለቡ ሶስተኛ ዋና አሰልጣኝ የሆኑት አቶ አሸናፊ በቀለ ዛሬ በይፋ መደበኛ ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡
ዋና አሰልጣኙ ዛሬ የመጀመሪያ ልምምዳቸውን ከተጫዋቾቹ ጋር ሲያደርጉ ለኢዜአ እንደገለጹት በሊጉ ሁለተኛው አጋማሽ ውጤታማ ለመሆን ከሥራ አመራርና ከደጋፊዎች ማህበር ጋር ተቀናጅተው ይሰራሉ፡፡
ክለቡ ያለበት ደረጃ በአዲስ መልክ ለሚረከብ አሰልጣኝ ተስፋ ሰጪ ባይሆንም፣ያሉት ደጋፊዎች ብዛትና አቅሙን በአግባቡ መጠቀም ከቻለ ፍሬያማ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ ብለዋል፡፡
የቡድን አንድነትን መመለስ፣ጠንካራና የአሸናፊነት ሥነ-ልቡና መገንባት፤ግብ በቀላሉ የማይቆጠርበት፣ከራሱ የግብ ክልል ይልቅ ጨዋታውን በተጋጣሚው ቡድን ሜዳ ላይ የሚጫወት ክለብ መስራት የትኩረት አቅጣጫቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ተሰናባቹ አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃን ጨምሮ ነባር አሰልጣኞችን በማሳተፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚተጉ አስታውቀዋል፡፡
በተከላካይ፣በመሃልና በአጥቂ ስፍራዎች የሚሰለፉ ሦስት ተጫዋቾች ካገኙ ለማስፈረም መዘጋጀታቸውን ዋና አሰልጣኙ ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው ያለውን ዕምቅ አቅም በመጠቀም ከ17ና 20 ዓመት በታች ያለውን ቡድን በማጠናከር ከክለቡ አልፎ ለአገር የሚተርፉ ተጫዋቾችን ለማፍራት ራዕይ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡
የአካባቢው ስፖርት ወዳድ ሕዝብ ክለቡን ስፖርታዊ ጨዋነት ጠብቆ በቋሚነት በመደገፍ ዘርፉን የሃብት ምንጭ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡
ክለቡ ውጤት በማጣቱ የተፈጠረውን ሁኔታ ለመለወጥ ከቀድሞ አሰልጣኝ ጋር በስምምነት መለያየታቸውን የተናገሩት ደግሞ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ሆሲሶ ናቸዉ፡፡
በክለቡ የውስጥ አሰራር ላይ የነበሩ የመልካም አስተዳደርና መሰል ችግሮችን ለማስቀረትና አሰራሩን ለማዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ግልጽ ማስታወቂያ ወጥቶ አሰልጣኝ መቀጠሩን አስታውቀዋል፡፡
አሰልጣኙ በሚመቻቸው መልኩ ያለውን አቅም በተደራጀ መልኩ በመጠቀም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
የክለቡ የደጋፊዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አንዱዓለም ሽብሩ በበኩላቸው በአገር አቀፍ ደረጃ ልምድ ያለው አሰልጣኝ መቀጠሩ ደጋፊዎች ማስደሰቱን ተናግረዋል፡፡
ክለቡ ስፖርታዊ ጨዋነት ስብዕና ያላቸው ደጋፊዎች ለማፍራት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ክለቡ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብ ለአሰልጣኙና ለተጫዋቾች ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ክለቡ በሊጉ የመጀመሪያው ዙር ካደረጋቸው ጨዋታዎች 15 ነጥብ በመሰብሰብ 13ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡ሦስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ፣በ12 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ በመውጣትና በመሸነፍ።
ክለቡ በሁለተኛው ዙር በቀጣዩ ወር በሚጀመረው የሊጉ ሁለተኛው ዙር የውድድር መርሐ ግብር ከስሑል ሽረ ክለብ ጋር በሶዶ ስታዲዬም እንደሚያከናውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያወጣው መርሃ ግብር ያሳያል፡፡