ለአድዋ ድል ከፍተኛ ሚና በነበረው የፉከራና ቀረርቶ እሴት ላይ እየሰራሁ ነው- ወሎ ዩኒቨርሲቲ

አዲስ አበባ የካቲት 26/2011  ለአድዋ ድል ከፍተኛ ሚና በነበራቸው የፉከራና ቀረርቶ እሴቶች ላይ እየሰራ አንደሚገኝ የወሎ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

የዩኒቨርቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን ለኢዜአ እንደተናገሩት ኪነ ጥበብ በተለይም ፉከራና ቀረርቶ በአድዋ ጦርነት ወቅት ዘማቹን ለማበርታትና ለመገሰጽ ሚናቸው የጎላ ነበር።

በጦርነቱም ከ150 በላይ አዝማሪዎች መዝመታቸውን በማንሳት፣ ቀረርቶና ፉከራ ሰራዊቱን በወኔ በመቀስቀስ ለድሉ የጎላ አስተዋጾ እንደነበራቸው አመልክተዋል።

'ባህሉን የማያውቅ ትውልድ የውሃ ላይ ኩበት ነው' የሚሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ባህል የማንነት መግለጫ መሳሪያ በመሆኑ ባህላችንን መሸጥ አለብን ይላሉ።

ከኢትዮጵያ ቱባ ባህሎት መካከልም በተለይም በአማራ ፉከራና ቀረርቶ ትልቅ ባህል መሆኑን ገልጸው፤ ወሎ ዩኒቨርሲቲ በእሴቱ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አነስተዋል።

ከክልሉና ከደቡብ ወሎ ዞን ጋር በመተባበር ቀደም ሲል ዝነኛ የነበረውን የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን ዳግም በማቋቋም እያጠናከረ መሆኑን፣ ባሕልን ለሰላምና ለልማት በሚል ሙዚቃዊ ድራማዎችና ሌሎች የኪነ ጥበብ ዘርፎች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በክልሉ ከሚገኙ 10 ዩኒቨርሲቲዎች ጋርም በባህል ላይ በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸው፤ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ዩኒቨርሲቲው ህዝብ ለህዝብ የሚያቀራርቡ ሶስት ሙዚቃዊ ድራማዎች ዩኒቨርሲቲው ማዘጋጀቱን አስታውሰዋል።

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ልዑል ዮሃንስ በበኩላቸው ቀረርቶና ፉከራ በአድዋም ሆነ በሌሎች ጦርነቶች ጠላትን ለመከላከል ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ የነበሩ ባህሎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ስለሆነም ቢሮው ከአድዋ ጋር የተያያዙ  ስፍራዎችን ማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትና አንድነትን የሚያጎሉ እንደ ፉከራና ቀረርቶ አይነት እሴቶችን ለማጉላት አቅዶ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ኪነ ጥበብ አገርን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ረገድ ሚናዋ የጎላ ነው ያሉት አቶ ልዑል፣ ከነዚህም መካከል ፉከራና ቀረርቶን ባህል እንዲጎለብት በተለያዩ ቦታዎች ዝግጅቶችን ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል።

ከነዚህም መካከል በመጭው ግንቦት ወር የሸዋ ባህልና ታሪክ ሲምፖዚየም በደብረ ብርሃን ከተማ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም