ሚኒስቴሩ የስንቄ ግጭት አፈታት ሥርዓት ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖረውና ለዓለም ለማስተዋወቅ እየሰራ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ሚኒስቴሩ የስንቄ ግጭት አፈታት ሥርዓት ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖረውና ለዓለም ለማስተዋወቅ እየሰራ መሆኑን ገለጸ
አዳማ የካቲት 26/2011 ባህላዊ የስንቄ ግጭት አፈታት ሥርዓት ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖረው ለማድረግና ለዓለም ለማስተዋወቅ እየሰራ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።
የሱዳን ልዑካን ቡድን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ኮፈሌ ወረዳ በኦሮሞ እናቶች የሚከወነውን ባህላዊ የስንቄ ግጭት አፈታት ሥርዓት ጎብኝቷል።
በሚኒስቴሩ የሴቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ወይዘሮ ወይንሸት ኃይለማሪያም እንዳሉት ሥርዓቱ ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖረውና ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዲያገኝ እየተሰራ ነው ።
በገዳ ሥርዓት ውስጥ ሴቶች በግጭት አፈታት ያላቸውን ሚና ለማስረዳት በአገሪቱ ያለውን ቱባ ባህል ለማስተዋወቅ ያሰችላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበርና በሚኒስቴሩ አስተባባሪነት የተዘጋጀው የሱዳን ልዑካን ቡድን ጉብኝት የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነት ሚናና እርቀ ሰላም በማውረድ ያላቸው ተሳትፎና ድርሻ የማሳወቅ ዓላማ እንዳለውም ዳይሬክተሯ አመልክተዋል።
አገሪቱ ችግሮችን በራሷ የምትፈታበት ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት እንዳላት ለጎረቤት አገሮችና ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ጥረት እንደምታደርግ የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አድማሱ ዋቅጅራ ናቸው።
ጉብኝቱ ከጎረቤት አገሮች ጋር ካለው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስር ባሻገር፤የጋራ ችግሮችን ለመፍታት በምናደርገው ሂደት ውስጥ የባህል ቁርኝት ሚናን ለማሳወቅና ልምድ ለመለዋወጥ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ሥርዓቱ በተለይም ሴቶች ነፃነታቸውን፣መብታቸውንና እኩልነታቸውን የሚያረጋግጡበት አንዱ ማሳያ ነው ያሉት አቶ አድማሱ፣ በባህሉ በፍትህ አሰጣጥና በአገር ገፅታ ግንባታ የሚኖረውን ፋይዳ ለሌሎች ለማሳወቅ እንደሚያስችል አስረድተዋል።
ሴቶች ከወንዶች እኩል በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች የመሳተፍና ውሳኔ የመስጠት መብት እንዳላቸው ያረጋግጣል ብለዋል።
ሥርዓቱ ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖረው ለማድረግና ለዓለም በማስተዋወቅ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት እንዲመዘገብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሰራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ በበኩላቸው ጎብኚዎቹ ከዘመናዊ የዳኝነት ሥርዓት በተጓዳኝ ሁሉንም የሚገዛውን ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ላይ ልምድ ለመቅሰም መምጣታቸውን ተናግረዋል።
የሱዳን ልዑካን ቡድን 23 ተሸላሚ ግንባር ቀደም ሴት አርሶ አደሮችን ያካተተ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ፣ በተለይም ከዳርፉር አካባቢ የተወጣጡ በመሆናቸው በአካባቢያቸው ግጭቶችን በራሳቸው ለመፍታት ልምድ ያገኙበታል ብለዋል።
ባህላዊ የግጭት መከላከልና አለመግባባት አፈታት ሥርዓት በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም አንዲረጋገጥ፣ልማትና እድገቷን እንዳስቀጠለም አስታውቀዋል።
የሱዳን ልዑካን ቡድን መሪ ፕሮፌሰር ሚኪ ሙሐመድ በበኩላቸው ሱዳንና ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገረ የባህል፣ቋንቋና ሃይማኖታዊ ትስስር ያላቸው ከመሆኑም ባለፈ በፖለቲካና ኢኮኖሚ መስኮች መልካም ግንኙነት የገነቡ አገሮች መሆናቸውን አስታውሰዋል።
በኦሮሞ እናቶች የሚከወነው ባህላዊ የስንቄ ግጭት አፈታት ሥርዓት ኢትዮጵያ ያላት አኩሪ የገዳ ሥርዓት ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሥርዓቱ አለመግባባቶች የሚፈቱበት ከመሆኑም ባለፈ፤ በሰላም እሴት ግንባታ ውስጥ የሴቶች ድርሻ ሚናን የተረዱበት መሆኑንም ተናግረዋል።