ቀጥታ፡

መንጌ ቤላሻንጉል የክለቦች እግር ኳስ ውድድር አሸናፊ ሆነ

አሶሳ ግንቦት 22/2010 የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የክለቦች እግር ኳስ ዓመታዊ ውድድር በመንጌ ቤላሻንጉል አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ በክልሉ ላለፉት አራት ወራት ሲካሄድ በቆየው የቤጉ ሊግ የእግር ኳስ ክለቦች ዓመታዊ ውድድር ላይ አስራ ሶስት የእግር ኳስ ክለቦች ተሳትፈዋል፡፡ መንጌ ቤላሻንጉል አሸናፊ የሆነው ትናንት በአሶሳ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል ሜዳ ለፍፃሜ በተደረጉ ውድድር ያሶ ከነማን ሶስት ለባዶ በመርታቱ ነው፡፡ ሶጌ ከነማ ደግሞ በለስ ከነማን  ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት አሸንፎ ውድድሩን በሁለተኛነት ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ ግልገል በለስ ከነማ በውድድሩ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል፡፡ በውድድሩ ከአንድ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ ክለቦች ከ35 ሺህ እስከ 25 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡ የክልሉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ  አቶ ደርቤ ከበደ በውድድሩ እስከ አራተኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁት ክለቦች በመጪው ሐምሌ ወር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጀው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ላይ  ቤኒሻንጉል ጉሙዝን ወክለው እንደሚሳተፉም አስታውቀዋል፡፡ በሊጉ ተሳታፊ ክለቦች መካከል የተሻለ ፉክክር ቢስተዋልም በውድድሩ ሂደት ያጋጠሙ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደሎች እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡ "የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር በተስተዋለባቸው ክለቦች ላይም አስተማሪ እርምጃዎች ተወስደዋል "ብለዋል፡፡ ሊጉ ከተጀመረ የሶስት ዓመታት እድሜ ብቻ ያለው በመሆኑ የሊጉ ተሳታፊ ክለቦችን ቁጥር በቀጣይ ዓመት ወደ አስራ ስድስት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ክለቦቹን ለማጠናከርም ፌዴሬሽኑ የሚሰጠው ሙያዊ ድጋፉን እንደሚቀጥልም አቶ ደርቤ አመልክተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም