የአጼ-ቴዎድሮስ ሽሩባ ና ሌሎች ቅርሶችን የሚያስመልስ የልኡካን ቡድን ወደ አንግሊዝ ሊላክ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአጼ-ቴዎድሮስ ሽሩባ ና ሌሎች ቅርሶችን የሚያስመልስ የልኡካን ቡድን ወደ አንግሊዝ ሊላክ ነው

አዲስ አበባ የካቲት 26/2011 የኢትዮጵያ መንግስት የአጼ ቴዎድሮስ መለያ የሆነው ሽሩባ ፀጉራቸውን ጨምሮ ሌሎች የአገሪቱ ቅርሶችን ለማስመለስ ቅርሶቹ ወደሚገኙበት እንግሊዝ አገር የልኡካን ቡድን ሊላክ መሆኑ ተገለፀ።
በመጪው መጋቢት 9 ቀን 2011 ዓም ወደ ለንደን የሚያቀናው የልኡካን ቡድን የሚመራው በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ነው።
አጼ-ቴዎድሮስ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1968 መቅደላ ላይ ለእንግሊዝ ወታደሮች እጅ አልሰጥም ብለው ራሳቸውን እንደሰዉ የታሪክ ድርሳናት ይገልፃሉ።
የአፄውን በዚህ መልኩ ማለፍ ተከትሎም በርከታ የኢትዮጵያ ቅርሶች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከአገር ሸሽተው በተለያዩ የአውሮፓ አገራት እንደሚገኙ ይታወቃል።
በኢንግሊዝ አገር የሚገኝ ''ናሽናል አርሚ '' የተሰኘ ሙዚየም ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በድረ-ገጹ ላይ የአጼውን ፀጉር ምስል ማሰራጨቱ፤ በአውደ-ርእይ ላይም ለህዝብ ማቅረቡ ብዙዎችን አስቆጥቶ እንደነበርም ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግስት ቅርሱ ወደአገር ቤት እንዲመለስ ጥረት መጀመሩን ነው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛሀኝ አባተ ለኢዜአ የተናገሩት።
ሚኒስትሩ በኢንግሊዝ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመሆን የአፄውን ፀጉር ለማስመለስ በቀረበው ጥያቄ መሰረት ብሪታኒያ ከ150 ዓመት በፊት የተወሰደውን ይህንን ሽሩባ ፀጉር ለመመለስ ፍቃደኛ መሆኗን አክለዋል።
በዚህም መሰረት በመጪው መጋቢት ወር ቅርሱን ለመረከብ ወደስፍራው አንድ የልኡካን ቡድን እንደሚያቀና ገልጸዋል።
ሌሎች ቅርሶችም በሚመለሱበት መንገድ ላይ ቡድኑ ይመክራልም ብለዋል።
በኢንግሊዝ አገር የሚገኙት በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶች እንዲመለሱ ላለፉት ዓመታት በደብዳቤ እየቀረበ ያለው ጥያቄ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት አቶ ገዛሀኝ።
በኢንግሊዝ አገር ህግ ከሙዚየም የሚወጡና የማይወጡ ቅርሶች ተብለው የተቀመጡ ቅርሶች መኖራቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ከሙዚየም ወጥተው የማይሰጡ የተባሉትን የኢትዮጵያን ቅርሶች በከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለማስመለስ የተቻለው ሁሉ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
እዛው በእንግሊዝ የሚገኘው የአጼ ቴዎድሮስ ልጅ የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ አፅም ለኢትዮጵያ ተመልሶ እንዲሰጥ የተደረገው ጥረትም እየተሳካ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የልኡሉ አፅም የዘረ-መል (ዲ ኤን ኤ) ምርመራ ከአባትየው ፀጉር በመውሰድ በማካሄድ የአፅሙን ማንነት የማረጋገጡ ተግባር በሂደት ላይ መሆኑም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ቅርሶች በአብዛኛው በኢንግሊዝ፣ በጀርመንና በጣልያን አገር የሚገኙ ሲሆን ወደ አገር ቤት ለማሰመለስ በአገራቱ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በኩል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል።