በአፄ ቴዎድሮስ ሐውልት ላይ ጉዳት ያደረሰችው ግለሰብ የአምስት ዓመት ጽኑ እስራት ተፈረደባት - ኢዜአ አማርኛ
በአፄ ቴዎድሮስ ሐውልት ላይ ጉዳት ያደረሰችው ግለሰብ የአምስት ዓመት ጽኑ እስራት ተፈረደባት
ጎንደር የካቲት 25/2011 በጎንደር ከተማ በሚገኘው የአፄ ቴዎድሮስ ሐውልት ላይ ጉዳት ያደረሰችው ግለሰብ በአምስት ዓመት ጽኑ እስራት መቀጣቷን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፍትህ መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያው የወንጀል ዐቃቤ ሕግ አቶ ድረስ ዘለለው ለኢዜአ እንደተናገሩት ቅጣቱ የተላለፈባት ነዋሪነቷ በጎንደር ከተማ በሆነው በወይዘሮ መንደሬ እያዩ አባተ ላይ ነው፡፡
ግሰሰቧ የካቲት 5 ቀን 2011 ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ30 ሲሆን፣ ፒያሳ አደባባይ ላይ የቆመውን ሐውልት ቀኝ እጅ ጎራዴ ላይ ጉዳት ማድረሷ በሦስት ምስክሮች በመረጋገጡ ነው፡፡
ግለሰቧ በወንጀል ሕግ ቁጥር 690 ንዑስ ቁጥር ሁለት የሕዝቦች የጋራ ሐውልት በሆኑ ታሪካዊ ቅርሶች ላይ ጉዳት በማድረስ የተደነገገውን አንቀጽ ተላልፋ መገኘቷንም አመልክቷል፡፡
ተከሳሿ በቀረበባት ክስ በፍርድ ቤት ወንጀሉን አልፈጸምኩም በሚል ክዳ ብትከራከርም ዐቃቤ ሕግ ያቀረበባትን ማስረጃን ባለማስተባበሏ ቅጣቱ ተወስኖባታል፡፡
የጎንደር ከተማ ፍርድ ቤት ግለሰቧ የቤተሰብ አስተዳዳሪና ከዚህ ቀደም የወንጀል ሪከርድ የሌለባት መሆኑን በቅጣት ማቅለያነት ተይዞላታል፡፡
ግለሰቧ የፈጸመችው ወንጀል እስከ 15 ዓመት በሚደርስ እስራት የሚያስቀጣ ቢሆንም፤ ፍርድ ቤቱ ማስረጃዎቹን በቅጣት ማቅለያነት እንደያዘላት ዐቃቢ ሕጉ አስረድተዋል፡፡
የከተማው ነዋሪዎች በሐውልቱ ላይ የደረሰውን ጉዳት በማስተባበር መልሰው እንደሰሩት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር አስታውሷል፡፡