በኢትዮጵያ ዘላቂ የከተሞች ዕድገት ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ አውደ ጥናት ነገ በአዲስ አበባ መካሄድ ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዘላቂ የከተሞች ዕድገት ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ አውደ ጥናት ነገ በአዲስ አበባ መካሄድ ይጀምራል
አዲስ አበባ የካቲት 26/2011 በኢትዮጵያ ዘላቂ የከተሞች ዕድገት ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ አውደ ጥናት ነገ በአዲስ አበባ መካሄድ ይጀምራል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ያዘጋጀው አውደ ጥናት "ለዘላቂ የከተማ እድገት ሽግግራዊ አመራር" በሚል መሪ ቃል እስከ የካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ይካሄዳል።
በኢትዮጵያ በሁሉም ደረጃ ውጤታማ፣ ተጠያቂነት የሰፈነበትና ሁሉን አቀፍ የሆነ የከተማ አስተዳደር ስርአት ለመገንባት ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከር የአውደ ጥናቱ ዋንኛ አላማ እንደሆነ በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
የከተማ ከንቲባዎችና አመራሮች ዴሞክራሲያዊ የሆነ መልካም የከተማ አስተዳደር ለመገንባት በዚሁ የግንባታ ሂደት የከተማ ነዋሪዎች በንቃት ተሳታፊ እንዲሆኑ በሚሰራው ስራ ስለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረግም አውደ ጥናቱ ትኩረት የሚያደርግበት ጉዳይ ነው።
የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የማይክሮ ኢኮኖሚና አስተዳደር የስራ ክፍል የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኦፊሰር ሚስ ኢውኒስ አጃምቦ ''አውደ ጥናቱ አመራሮችና ሲቪል ሰርቫንቶች በዘላቂ የከተማ ልማት አስተዳደር ላይ ያላቸው ክህሎት እንዲዳብርም አስተዋጽኦ ያደርጋል'' ብለዋል።
ተጠያቂነት የሰፈነባቸው ተቋማት መገንባትና የፍትህ ስርአቱን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ በሚል በዘላቂ የልማት ግቦች የተቀመጠው 16ኛ ግብ እንዲሳካ አመራሮችና ሲቪል ሰርቫንቶች መወጣት ስለሚገባቸው ሚና ላይ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በአፍሪካ የከተማ እድገት እንዲረጋገጥ ጠንካራ የህዝብ ተቋማቶችና መዋቅሮች፣ የአቅም ግንባታና ጠንካራ ተቋማዊ አሰራር ሊኖር እንደሚገባም አመልክተዋል።
ሽግግራዊ አመራር ለ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች መሳካት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትና በዚህም ረገድ መሪዎች አስፈላጊውን አቅምና አመለካከት በመያዝ የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ መስራት እንደሚገባቸውም ጠቅሰዋል።
''በ2030 የዘላቂ የልማት ግቦች ውስጥ መዋቅራዊ ለውጥ'' በሚል የተቀመጠው ሀሳብ ውስጥ በህዝብ አገልግሎት ላይ ያለው አመለካከት ከተቀየረ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ሰራተኞቻቸው የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ከተሞችና የህዝብ አሰፋፈር የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ቁልፍ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በዘላቂ ልማት ግብ ውስጥ 11ኛው ግብ የከተሞች መስፋፋት ለዘላቂ ልማቱ መሳካት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትና ከተሞችንና የህዝብ አሰፋፈርን ሁሉን አቀፍ፣ ደህንነቱ የተረጋገጠ፣ የማይበገርና ዘላቂ መሆን እንዳለበትም በግልጽ እንዳስቀመጠ ነው ሚስ ኢውኒስ ያስረዱት።
በከተሞች መስፋፋት ውስጥ ዜጎችን በተለይም በከፍተኛ ሁኔታ የአደጋ ተጋላጭነትና ትኩረት የተነፈጋቸው ማህበረሰቦች አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2037 በከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ቁጥር 42 ነጥብ 3 ሚሊዮን ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል።
በተጠቀሰው ጊዜ በከተማ የሚኖረው ህዝብ ብቻ ሳይሆን ከተሞች የሚይዙት መሬትና በከተሞች መጨመር ምክንያት ወደ ከተማነት የሚቀየሩ የገጠር ቦታዎች በስፋት እንደሚጨምሩም ተጠቅሷል።
በዚህ ረገድ አሁን በኢትዮጵያ ያለው የከተሞች መስፋፋትና የከተማ ልማት በጅምር ላይ ያለ እንደሆነና ወደፊት ለተያዘው ለኢትዮጵያ እድገት፣ የኢንዱስትሪና ዘላቂ ልማት አጀንዳ ወሳኝ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ኮሚሽኑ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉን አቀፍና ዘላቂ የከተማ ልማትን በከተማ ልማት አጀንዳ ውስጥ ዋንኛ ግቡ አድርጎ እንዳስቀመጠና የከተሞች መልካም አስተዳደርና የአቅም ግንባታ መንግስት ስትራቴጂካዊ ትኩረት የሰጠባቸው ቀዳሚ ጉዳዮች እንደሆኑም ተመልክቷል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ከተሞች ማህበር ለሶስት ቀናት የሚቆየውን ዓለም አቀፍ አውደ ጥናት በትብብር ያዘጋጁ አካላት ናቸው።