ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አዲስ ኮሚሽነር እጩ መጠቆም ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ  የካቲት 26/2011ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አዲስ ኮሚሽነር ለመሰየም እንዲቻል ከመጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለዚህ ዓላማ የተቋቋመ ኮሚቴ ጥቆማ እንደሚቀበል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አስታወቁ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰየመው 14 አባላት ያሉት የኮሚሽነር እጩ አቅራቢ ኮሚቴ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነርነት  የሚቀርቡ እጩዎችን  ከአራት ቀናት በኋላ በጥቆማ መቀበል ይጀምራል።

በአፈ ጉባኤው የሚመራው ኮሚቴ ቀደም ብሎ ባካሄደው ስብሰባ የእጩዎችን መመዘኛ መስፈርት፣ የስራ መመሪያና በሌሎች ተያያዥ የአሰራር ስርዓቶች ላይ በመምከር አቅጣጫ አስቀምጧል። 

በዚሁ መሠረት ኮሚቴው ጥቆማዎችን የሚቀበለው ከህዝቡ፣ ከተቋማት፣ ከክልል መንግስታትና የከተማ አስተዳደሮች መሆኑን አፈ ጉባዔው ዛሬ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። 

ጠቋሚዎች በእጩነት የሚያቀርቧቸው  በዜግነት ኢትዮጵያዊ፣ እድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ የሆኑ፣ ለህገ መንግስቱ ተገዥዎች፣ ለሰብአዊ መብት ጥሰት የሚቆረቆሩ፣ በህግ ወይም በሌላ አግባብ ባለው ሙያ የሰለጠኑ ወይም ሰፊ ልምድና እውቀት ያካበቱ የሚሉትን መስፈርቶች እንደሚያሟሉ ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የዛሬ 19 ዓመት በአዋጅ ሲቋቋም በህገ-መንግስቱና አገሪቷ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ላይ የተዘረዘሩት መብቶች በአግባቡ መከበራቸውን መከታተል ዋና ዓላማዎቹ አድረጎ ነው። 

ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ በእስካሁኑ የሥራ አፈጻጸሙ "የዜጎችን የሰብዓዊ መብት ጥበቃ በወጉ ሲያስከበር አልነበርም" በሚል በብዙዎች ይተቻል።

መንግስትም ይህንን በመገንዘብ የአገሪቷን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ኃብታዊና ሌሎች ዴሞክራሲን የሚያጎለብቱ ቁልፍ ጉዳዮችን ያካተተ አጠቃላይ የለውጥ ተግባራት ከወራት በፊት መጀመሩን ያስታወሱት አፈ ጉባኤው፤ ከእነዚህም መካከል የሰብአዊ መብት ጥበቃ ጉዳይ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት የኮሚሽኑን የመወሰን አቅሙን ለማሳደግ የህግ ማዕቀፍ፣ አጠቃላይ የአሰራር ስርዓትና ተያያዥ ጉዳዮችን መሰረት ያደረገ የሪፎርም ሥራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ እንደገለጹት፤ ሪፎርሙ በሚጠይቀው ብቃት፣ ክህሎትና ትጋት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚያስጠብቅ ኮሚሽነር ለመሰየም የሚያስችል ተግባር ተጀምሯል።  

መስፈርቶቹ የተዘጋጁት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተመክሮዎችን በማካተትና የመላው ህዝብን ተሳትፎ ማጠናከር በሚያስችል መንገድ ከዚህ በፊት ከነበሩት በተለየ መንገድ ለትምህርት ዝግጅት፣ የሥራ ልምድ፣ የጥቆማ ተሳትፎና ሌሎች ጉዳዮች የተለየ ትኩረት መስጠቱም ተመልክቷል።

በበፊቱ አሰራረ ከዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ጀምሮ መወዳደር ይቻል እንደነበር ያመለከቱት አፈ ጉባኤው፤ የትምህርትና የሥራ ልምድን በተመለከተ አሁን የተቀመጡት መስፈርቶች ከከዚህ ቀደሙ በተለየ ለዘርፉ የሚመጥን የትምህርት ደረጃና የካበተ የሥራ ልምድ ትኩረት ተሰጥቷል።

በተለይም በህግ የመጀመሪያ ዲግሪና በላይ፣ ከዚህም አልፎ በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ሁለተኛ ዲግሪ ላለው ቅድሚያ ይሰጣል ነው ያሉት አፈ ጉባኤው። 

ጥቆማው ከተጠናቀቀ በኋላም ኮሚቴው በቀረበለት መስፈርት መሰረት እጩዎችን ይለያል፤ አጠቃላይ ሂደቱን የተመለከተ ሪፖረት በማዘጋጀትም በመጪው ሚያዚያ 5 ቀን 2011 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ  የኮሚሽነሩን ምርጫ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል። 

የምርጫ ሂደቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት በህዝብ ዘንድ ያለውን ተአማኒነት ለማጠናከር፣ የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት ተወጥቶ የአገሪቷን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ማሻሻል የሚያስችል ቁመና እንዲኖረው ለማደረግ በሚያስችል መንገድ እንደሚከናወን የጠቀሱት አፈ ጉባኤው ፤ የሚመረጠው ዕጩም አምስት ዓመታት የሥልጣን ዘመን እንደሚኖረው አስረድተዋል።

ህዝቡ የተቀመጡትን መስፈርቶች በማጤን በላቀ ትጋት በጥቆማ እንዲሳተፍ አፈ ጉባኤው ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሚቴ የተውጣጣው ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከፌዴሬሽን ምክር  ቤት፣  ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና  ከሁሉም እምነት ተቋማት መሆኑም በመግለጫው ወቅት ተጠቁሟል። 

በስልክ 0111241036፣ በፋክስ 0111241060፣ በኢሜል hprhumanright@gmail.com እንዲሁም በፖስታ ሳጥን ቁጥር 80001 ጥቆማውን ማከናወን ይችላል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም