አሜሪካ በኢትዮጵያ ለሚካሄደው ለውጥ ሙያዊ ድጋፍ እያደረገች መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
አሜሪካ በኢትዮጵያ ለሚካሄደው ለውጥ ሙያዊ ድጋፍ እያደረገች መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ የካቲት 26/2011 አሜሪካ በኢትዮጵያ የደኅንነት ዘርፉን ጨምሮ የሚካሄደውን የሪፎርም ተግባራት ሙያዊ ድጋፍ እያደረገች መሆኑ ተገለጸ።
የአሜሪካን የኮንግረስ አባል ካረን ባስ የተመራው የልዑክ ቡድን በኢትዮጵያ ለሦስት ቀን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ትላንት አዲስ አበባ ገብቷል።
የኮንግረስ አባሏ ካረን ባስ ትናንት ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ አሜሪካን የተለያዩ ሙያዊ ድጋፍ እንድታደርግላት አስቀድማ መጠየቋን ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎም አሜሪካ በኢትዮጵያ የደህንነት ዘርፉን ጨምሮ የሚካሄደውን ለውጥ ከግብ ለማድረስ አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ እያደረገች መሆኑን ነው ያስረዱት።
በሚቀጥለው ዓመት በኢትዮጵያ ለሚካሄደው ምርጫም አሜሪካ ሙያዊ እገዛ አንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
ከስድስት ወራት በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውን የገለጹት ካረን ባስ በአገሪቷ እየተካሄደ ያለው ለውጥ እንዳስደሰታቸውና ቀጣይነት እንዲኖረው መሰራት አለበት ብለዋል።
ለውጡን ተከትሎም በአሜሪካ ለበርካታ ዓመታት ወደ አገራቸው ያልተመለሱ የኢትዮጵያ ዲያስፖራም ወደ አገራቸው እየተመለሱ መሆኑን መታዘባቸውን ጠቁመዋል።
በኮንግረስ አባልነታቸው ለስምንት ዓመታት የአሜሪካ የንግዱ ማኅበረሰብን በተመለከተ መሥራታቸውን ጠቁመው በኢትዮጵያ በኢንቨስትመት እንዲሰማሩ እሰራለሁም ነው ያሉት።
በተለይም ደግሞ በትራንስፖርት፣ በመንገድ፣ በኤርፖርትና በሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፎች እንዲሳተፉ ነው የጠቆሙት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በአገር ውስጥ ከሚሰሩት የለውጥ ተግባራት ባሻገር ምስራቅ አፍሪካን ለማዋሃድ የሚሰሩት ሥራ የሚበረታታ መሆኑንም ካረን አንስተዋል።
አሜሪካ በኤርትራ በተለይም በሰብዓዊ መብት አያያዝ፣በዴሞክራሲና በሌሎች ጎዳዮች ላይ ሪፎርም እንዲካሄድ አየሰራች መሆኗንም ገልጸዋል።
በኤርትራ በእስር ላይ የሚገኙ የአሜሪካን ዜጎችና ሌሎች ዜጎችም በቅርቡ ይፈታሉ የሚል አምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በሱዳን ያለውን የፖለቲካ ሁኔታም አሜሪካ በቅርበት እየተከታተለች መሆኑን አስረድተዋል።