ቀጥታ፡

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ትኩረት የሚሹ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን አመለከተ

አዲስ አበባ የካቲት 25/2011 ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ትኩረት የሚሹ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አመለከተ።

ተቋሙ በአገሪቷ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለሟቋቋም የሚደረገውን ጥረትና ለችግር የተጋለጡ የጎዳና ተዳዳሪዎች ላይ በተደረገው ቁጥጥር የተገኙ ግኝቶችና መፍትሄዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።

ተፈናቃዮችን መልሶ በማቋቋም ሂደት አፈፃፃም ላይ በተደረጉ የቁጥጥር ስራዎች ግኝት እንዳመላከተው ተፈናቃዮች መልሶ በማቋቋም ሂደት ውስጥ ችግር ለመቅረፍ በርካታ ሥራ መሰራት አለበት።   

ግኝቱን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የተቋሙ የቁጥጥርና ጥናት ዳይሬክተር አቶ አዳነ በላይ የምግብና ቁሳቁስ አቅርቦትና ስርጭት፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ዋስትና መስጠትና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ከአመለካከትና ግንዛቤ፣ ከስነ-ልቦና፣ ከተረጂነት መንፈስ፣ ከወጥነት ያለው አሰራርና የቅንጅት ስራን ከማጠናከር አንጻር ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

''ተፈናቃዮች ከተጠለሉባቸው አካባቢዎች ማህበረተሰብ ጋር ተቀናጅተው የሚሰሩበትን አቅም  ማሳደግ፣ የተሟላና ዝርዝር መረጃ ማደራጀት፣ የህግ  የበላይነትን በማስፈን አጥፊዎች ተለይተው እንዲያዙና ውሳኔ እንዲተላለፍ ማድረግ ትኩረት ይጠይቃል'' ብለዋል።

የተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሀይሌ በበኩላቸው በተለያየ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችና የጎዳና ተዳዳሪዎችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት ባለድርሻ አካላትን አቀናጅቶ በትኩረት መስራት እንዳለበት አመላክተዋል።

በአገሪቱ የነበረው የፖለቲካ ምህዳር ሁሉን አሳታፊ ያልነበረ በመሆኑ የተነሳ የህዝቡን መስተጋብር በማዛነፍ በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢ ብዙዎችን ሊያፈናቅል የቻለ ክስተት ማጋጠሙን ተናግረዋል።

በአንዳንድ አካባቢ በተነሱ ግጭቶችና የሚኖሩባቸው ቤቶች በመፍረሳቸው ሞትና መፈናቀል እንዳስከተለም ገልጸዋል።

ከዜጎች መፈናቀል በተጓዳኝ በአገሪቷ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እየደረሰ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል።

ችግሮቹን ለመፍታት መንግስት ግብረ-ኃይል አቋቁሞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ቢያደርግም እስካሁን በተሰሩት ስራዎች አጥጋቢ ውጤት ማስመዝገብ አለመቻሉን ጠቁመዋል።

መንግስት ችግሮቹን ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት ባለድርሻ አካላት ተሳትፈው የተቀናጀ ስራ መስራት የችግሩን ስፋት ሊቀንስ እንደሚችል ገልጸዋል።

ተቋሙ ለችግር የተጋለጡ የጎዳና ተዳዳሪዎች ላይ ያደረገው የቁጥጥር ግኝት በተመለከተ ገለጻ ያደረጉት በተቋሙ የሴቶችና ህፃናት ዳይሬክተር አቶ አበራ ኽርቃታ ዜጎችን ከጎዳና ተዳዳሪነት ለማላቀቅ እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል።

ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በላይ እና በታች የሆኑ ጎዳና ተዳዳሪዎችን በሁለት በመክፈል የተለያየ ተግባር እየተከናወነ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንጻር አመርቂ ውጤት አልመጣም።

በተለይም ከጎዳና ላይ እየተነሱ ዳግም ወደጎዳና የሚመለሱ ሰዎች ችግሩን የመፍታት ጥረት አስቸጋሪ እንዳደረገው የገለጹት አቶ አበራ ''ከአንድ ጊዜ እስከ ሰባት ጊዜ ከጎዳና ተነስተው የተመለሱ ዜጎች አሉ'' ሲሉ አብራርተዋል።

ለጎዳና ተነሺዎች የሚሰጠውን የማገገሚያና የስልጠና ጊዜ በቂ ማድረግ፣ ቅንጅታዊ አሰራርንና የስራ ድግግሞሽን ማስቀረት፣ ሰልጣኞች ወደ ስራ ሲሰማሩ የሚጠየቀውን የካፒታል መነሻ 10 በመቶ ማስያዣ በሌላ አሰራር መተካት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ለጎዳና ተዳዳሪዎች ቤንዚንና ማስቲሽ በሚያቀርቡ ግለሰቦች ላይ ተገቢና አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ የህግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ ማድረግ፣ የጎዳና ተዷዷሪዎች የቅበላና የማገገሚያ ተቋማትን ማቋቋም በትኩረት ሊሰራ የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አብራተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ተፈናቃዮችንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን ችግር በዘላቂነት መፍትሄ መስጠት ተገቢ መሆኑን ጠቁመው በጊዜያዊነት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ወጥነት ባለው መልኩ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

አቶ ፀጋዮ ወጁ የተባሉት አስተያየት ሰጪ ከጎዳና የሚኒሱ ህፃናትን ወደ ቤተሰቦቻቸው መቀላቀል ብቻ ሳይሆን የሚኖሩበት ማህበረሰብም እንዲደግፍና እንዲከታተል የሚያደርግ አሰራር መከተል ተገቢ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሰኒያ ሳኒ ደግሞ ''ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ችግር ለመቅረፍ በጥናት፣ የአንድ ክልል እድገት ለሌላው እድል መሆኑን መግለጽና ህዝቡን በሚያገጩት ላይ ህብረተሰቡን ማዕከል ያደረገ ስራ መስራት ያስፈልጋል'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም