የካቲት 11 ለሰላምና ዴሞክራሲ መሰረት የተጣለባት እለት ነች - የህወሓት ም/ሊቀመንበር

አዲስ አበባ የካቲት 24/2011 በኢትዮጵያ "ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የሚቻለው ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ ሲከበሩ" መሆኑን ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እንደሚያምን ምክትል ሊቀመንበሯ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር ገለፁ።

ህወሓት የተመሰረተበት 44ኛ ዓመት ክብረ በዓል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች በተገኙበት ተከብሯል።

በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር ወይዘሮ ፈትለወርቅ እንዳሉት በአገሪቷ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ የሚቻለው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ ሲከበሩ ብቻ መሆኑን ድርጅቱ ያምናል።

ለዚህም ድርጅቱ በኢትዮጵያ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉን ያስታወሱት ወይዘሮ ፈትለወርቅ፤ ለእነዚህ እሴቶች መረጋገጥ በተከፈለው መስዋእትነት ደርግ ሊደመሰስ እንደቻለ ተናግረዋል።

የካቲት 11 በኢትዮጵያ ሰላምና ዴሞክራሲን ለማስፈን ትግል የተጀመረበት ታሪካዊ እለት መሆኑን ምክትል ሊቀመንበሯ አስታውሰዋል።

የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ረጅም ሂደትን የሚጠይቅ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ፈትለወርቅ፤ ባለፉት ዓመታት ቀላል የማይባሉ አመርቂ ለውጦችና ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

እንደ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገለፃ ኢህአዴግ ባለፉት 27 ዓመታት አንፀባራቂ ድሎችን ማስመዝገብ ቢችልም የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል ግን መሰናክሎች እየገጠሙት ይገኛሉ።

ባለፉት ጊዜያት ለተመዘገቡት ድሎችም ይሁን ጥፋቶች ሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የሚጋሩት መሆኑንም አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው የዛሬ 44 ዓመት በአገሪቷ ላይ ሲደረግ የነበረው ግፍና በደል መሸከም አቅቷቸው ለአገራዊ አንድነት ሲሉ ዋጋ የከፈሉበት ነው።

አሁንም በዚህ የለውጥ ሽግግር ወቅት የሚደመር እየተደመረ የሚቀነስ ደግሞ እየተቀነሰ ለኢትዮጵያዊያን አንድነት መጠናከር መስራት ይገባል ብለዋል።

በትግሉ ወቅት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ ሊደረግ ይገባል ያሉት ከንቲባው ይህም እርዳታ ሳይሆን ታሪክ እንደይረሳና ውለታቢስ ላለመሆን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም