ቀጥታ፡

ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ሕብረተሰቡና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ ትግልን ሊከተሉ ይገባል----የፓርቲ አመራሮች

ሆሳዕና የካቲት 24/2011 ሀገራዊ ለውጡን ወደታችኛው አመራር በማድረስ አጠናክሮ ለማስቀጠል ህብረተሰቡና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ ትግልን ሊከተሉ እንደሚገባ የኢሶዴፓና የመድረክ አመራሮች ገለጹ።    

የፓርቲዎቹ አመራሮች ትናንት በሀድያ ዞን ሆሳዕና ከተማ ከአባሎቻቸው ጋር ተወያይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ "የ27 ዓመታት የሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ከየት ወዴት" በሚል ርዕስ አጭር የውይይት መነሻ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ በጽሁፋቸው በ27 ዓመት የትግል ቆይታቸው ከኢህአዴግ አጋጥሞኛል ያላቸውን አንስተዋል።

"በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለኢህአዴግ ልዩ መሪ ሆነው መቀመጣቸው በትግል ለቆየነውም አካላት ጭምር የተሻለ አማራጮችን እንድንጠቀም አድርገውናል" ብለዋል፡፡

"በላይኛው አመራር ደረጃ ለውጡን ተቀብሎ የማስኬድ ሁኔታ ቢኖርም ከዞን እስከ ቀበሌ ባለው የታችኛው መዋቅር ለውጡን ተቀብሎ በማስኬድ በኩል ክፍተቶች አሉ" ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል ።

"ለውጡን ወደ ታችኛው መዋቅር በማድረስ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ የህበረተሰቡና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ ትግል ያስፈልጋል" ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ለውጡ መሬት ካልረገጠ ውጤታማ ስለማይሆን ፓርቲያቸው የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል ።

ኢህአዴግ ባለፉት 27 ዓመታት በተከተለው የፌዴራሊዝም ያልተማከለ የአስተዳደር ስርአት የሞግዚት አገዛዝ እንደነበር ያስታወሱት ደግሞ የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ናቸው ።

"የፌዴራሊዝም ስርዓት የተወሰኑ ችግሮችን ቢፈጥርም ከእርሱ የሚሻል አማራጭ የለም " ብለዋል ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና።

"ፌዴራሊዝም የህዝቦችን ውሳኔ መሰረት በማድረግ የጋራና የራስ አስተዳደር መፍጠር መቻል ነው" ያሉት ፕሮፌሰሩ አሁን ባለው ሁኔታ የለውጥ ሂደቱ መንታ መንገድ ላይ ተንጠልጥሎ መቅረቱን ተናግረዋል።

"በአሁኑ ወቅት የጠብ መንጃ አገዛዝ ቀርቷል" ሲሉም ፕሮፌሰር መረራ ጨምረው ገልፀዋል።

"ለውጡን ለማስቀጠል የኛ ሰላማዊ ትግል ወሳኝ ነው፣ ስለሆነም ሀድያና ኦሮሞው በጋራ በመሆን ለውጡን እናስቀጥላለን" ብለዋል፡፡

ፕሮፌሰር መረራ እንዳሉት እንደ መድረክ የጋራ ሀገር ለመፍጠር እንጥራለን ።

በሀድያ ዞን የኢሶዴፓ ሊቀመንበር አቶ አጫሞ ቦቄ በበኩላቸው ሁሉም ፓርቲዎች ጥረታቸው ለሀገራዊ ለውጡ መሳካት በመሆኑ በሰላማዊ አቅጣጫ ትግላቸውን ሊቀጥሉ እንደሚገባ አመላክተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም