ሁሉንም የሚጠቅም ጠንካራ የፌዴራል ስርዓት መገንባት አስፈላጊ ነው---የፌዴሬሽን ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ሁሉንም የሚጠቅም ጠንካራ የፌዴራል ስርዓት መገንባት አስፈላጊ ነው---የፌዴሬሽን ምክር ቤት
መቀሌ የካቲት 24/2011 በኢትዮጵያ ሁሉንም ፍትሃዊ ተጠቃሚ እና አሳታፊ የሚያደርግ ጠንካራ የፌዴራል ስርዓት መገንባት አስላፈጊ እንደሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሒም ገለጹ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የክልሎች የጋራ ምክክር መድረክ በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ ወይዘሮ ኬሪያ እንደተናገሩት የፌዴራል ስርዓቱ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ በሚችል መልኩ እንዲቀጥል ሁሉም የድርሻውን መስራት አለበት።
በሃገሪቱ እየታየ ያሉ ችግሮች በዘላቂነት መፍታት የሚቻለውም ስርዓቱን ከአደጋ በመጠበቅ መጓዝ ሲቻል መሆኑን አስረድተዋል።
በምክክር መድርኩ ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ሩፋኤል ሽፋረ በበኩላቸው የህዝብ ራስ ምታት የሆነውን የመልካም አስተዳደር እጦት ችግር ለመፍታት ሁሉም በትጋት መስራት አለበት።
“ስለዚህ በህዝብ የተሰጠን ሃላፊነት ለህግ የበላይነት እንዲውል በማድረግ ለህዝብ የቆምንለትን ዓላማ ተግባራዊ ልናደርግ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።
በምክክር መድረኩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሠር ዶክተር ዮናስ አዳየ ”አክራሪ ጎሠኝነት በኢትዮጵያ” መነሻ ምክንያቶች፣ ያስከተለው ችግር እና መፍትሄዎች የሚል ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር አሰፋ ፍስሃ ደግሞ ” የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት መነሻ እሳቤው፣ የዜግነት መብትና የአገር ግንባታ” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረክ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳድር ምክር ቤቶችን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎች የመጡ 150 ያህል አፈ-ጉባኤዎች ፤ቋሚ ኮሚቴዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው ሌሎች አመራሮችና ምሁራን ተገኝተዋል።