ቀጥታ፡

የባይራ ኮይሻ ወረዳ ተመሰረተ

ሶዶ የካቲት 24/2011 በወላይታ ዞን የባይራ ኮይሻ ወረዳ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች በተገኙበት  ዛሬ በይፋ ተመሥርቷል፡፡

የወረዳው ዋና  አስተዳደሪ አቶ ዮሐንስ በየነ እንደገለፁት ወረዳው በአዲስ መልክ የተመሰረተው የህዝቡን የመልካም አስተዳደርና የልማት ተጠቃሚነት ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ እንዲቻል ነው ።

"የወረዳው መመስረት በህዝብ ዘንድ መተማመን በመፍጠር ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ይረዳል " ብለዋል ።

ወረዳው አዲስ የተደራጀ በመሆኑ የተጓደሉ ልማቶች እንዲሟሉለት ባለድርሻ አካላት ድጋፍ  እንዲያደርጉ ዋና አስተዳዳሪው ጠይቀዋል።

የወላይታ ዞን ተጠባባቂ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ መንግስት ተገቢና ሚዛናዊ ለሆኑ የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል ።

"የክልሉ መንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት የሚኖረውን ፋይዳ በማጥናትና በመረዳት ለቀረቡ አራት ተጨማሪ የወረዳ መዋቅር ጥያቄዎች በሰጠው ፍቃድ መሰረት ወረዳው በአዲስ መልክ ተመስርቷል" ብለዋል ።

ተጠባባቂ ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት የዞኑ አስተዳደር የወረዳውን አደረጃጀት ለማጠናከር አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል።

በወረዳው የበቅሎ ሰኞ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አበባ ታፈሰ " ከዚህ ቀደም ህዝቡ ከመንግስት የሚፈልገውን አገልግሎት ለማግኘት ብዙ ርቆ ስለሚሄድ ለገንዘብ፣ ለጊዜና ጉልበት ብክነት ይጋለጥ እንደነበር አስታውሰዋል።

"በአሁኑ ወቅት የወረዳው መመስረት ህዝቡ የሚፈልጋቸውን አገልግሎቶች በአቅራቢያው እንዲያገኝ ያስችለዋል" ብለዋል ።

የወላይታ ዞን በ16 ወረዳና በስድስት የከተማ አስተዳደሮች የተደራጀ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም