ጌታዘሩ ስፖርት ክለብ በሴቶች የቮሊቦል ውድድር አሸናፊ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
ጌታዘሩ ስፖርት ክለብ በሴቶች የቮሊቦል ውድድር አሸናፊ ሆነ
አዲስ አበባ የካቲት 24/2011 ከየካቲት 16 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ "ትኩረት ለሴቶች ቮሊቦል" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ በተካሄደው የቮሊቦል የአቋም መለኪያ ውድድር ጌታዘሩ ስፖርት ክለብ አሸናፊ ሆነ።
በውድድሩ ጌታዘሩ የስፖርት ክለብ፣የኢትዮጵያ ውሃ ስራዎችና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶ ስፖርተኞች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ውድድሩ እየተቀዛቀዘ የመጣው የሴቶች ቮሊቦል ትኩረት እንዲሰጠው በማሰብ ነው።
ስፖርቱ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል በሚባል መልኩ እየተዘወተረ ቢገኝም የሴቶች ቁጥር በክለቦች ደረጃ እየቀነሰ መጥቷል ያሉት ሃላፊው ችግሩን ለመፍታት ፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በሁለቱም ጾታዎች የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ እየተካሄደ እንደሚገኝና በዘንድሮው ዓመት የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ እስካሁን እንዳልተጀመረ ጠቅሰዋል።
በአቋም መለኪያ የተሳተፉትን ክለቦች ጨምሮ ወላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ እና አዳማ ከተማ አዲስ ተሳታፊ በፕሪሚየር ሊጉ ላይ ይሳተፋሉም ብለዋል።
ፌዴሬሽኑ ውድድሩን ከየካቲት 28 እሰከ መጋቢት 8 ቀን 2011 ዓ.ም በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ከሚካሄደው 3ኛው የመላ ኢትዮጵያ የሴቶች ጨዋታ በኋላ ለማካሄድ እቅድ መያዙንም ጠቁመዋል።
ትናንት ጌታዘሩ ስፖርት ክለብና ኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች ባደረጉት ጨዋታ ጌታዘሩ ስፖርት ክለብ በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
ውጤቱንም ተከትሎ ጌታዘሩ በሁለቱ ጨዋታዎች አምስት ነጥብ በመሰብሰብ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን ዋንጫ ተሸልሟል።
ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በአራት ነጥብ ሁለተኛ ኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች ያለ ምንም ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቀዋል።
የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የውድድርና ስነ ስርአት ኮሚቴ አባል ወይዘሮ አሚና ሽኩር የዋንጫውን ሽልማት ለጌታዘሩ ስፖርት ክለብ አበርክተዋል።