ቀጥታ፡

የበለጸገች ሀገር ለመገንባት ወጣቶች ከአድዋ ጀግኖች አንድነትና ጽናትን ሊላበሱ ይገባል.... የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ

ድሬዳዋ  የካቲት 24/2011 ወጣቶች ከአድዋ ጀግኖች አንድነትና ጽናትን ተምረው በተባበረ ክንድ የበለፀገች ሀገር ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ተግተው ሊሰሩ እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ።

በድሬዳዋ በተከበረው 123ተኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ለይ የተገኙ ነዋሪዎች በበኩላቸው የሀገሪቱን ሰላም በመጠበቅ ከድህነት የተላቀቀች ሀገር ለመገንባት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

"የአድዋ ድል የአንድነታችን ማህተም ነው"  በሚል መሪ ሃሳብ  በድሬዳዋ በየደረጃው የሚገኙ ነዋሪዎች በዓሉን በፓናል ውይይት አክብረዋል።

በበዓሉ ላይ የታሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አብደላ አህመድ የአድዋ ድል ሁሌም የኢትዮጵያዊያን የአንድነት መገለጫና የኩራት ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል።

"በአሉን ከመዘከር ባለፈ ወጣቱ አንድነትና ጽናቱን በማጠናከር የአድዋ ጀግኖች ያስረከቡንን ነጻነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ሰላምና ዕድገቷን ለማረጋገጥ ሌት ተቀን መስራት ይገባዋል" ብለዋል።

ወጣቱ ድህነትን አምርሮ በመታገል የበለፀገች ሀገር ለመገንባት ከምንግዜውም በላይ መረባረብና መትጋት እንዳለበትም ነው ጥሪ ያቀረቡት።

ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል አያታቸውን  በአድዋ ጦርነት ያጡት አዛውንቱ አቶ መሐመድ ዳሞታ ድሉ በትውልድ ውስጥ የአሸናፊነት መንፈስ ያሰረጸ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት መሆኑን ተናግረዋል።

"የዛሬ ወጣቶች ጀግኖች አባቶች ያስረከቧቸውን ነጻነትና አንድነት በመጠበቅ ኢትዮጵያን ወደ እድገት ጎዳና መምራት አለባቸው" ብለዋል

ጀግኖች አባቶች በአድዋ ጦርነት ያሳዩት መተባበር፣ አንድነትና ፅናት ለአሁኑ ትውልድ ትልቅ ትምህርት መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሻንበል ጌታቸው ማሞ ከምስራቅ አየር ኃይል ምድብ ናቸው።

"እኔና የሥራ ባልደረቦቼ  የሀገሪቱን ነጻነትና ሉአላዊነት በማስከበር በአድዋ የተከፈለውን መስዋዕትነት ለመድገም  ዝግጁ ነን" ብለዋል።

" ሴቶች በአድዋ ጦርነት ለተገኘው ድል ከፍተኛ ኃላፊነት እንደነበራቸው ሁሉ እኛም የአካባቢያችንና የሀገራችንን ሳላም በመጠበቅ የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ከዳር እናደርሳለን " ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ደራርቱ ረመዳን ናቸው።

ወጣት ናትናኤል ከበደ በበኩሉ የዛሬው ትውልድ ከጀግኖች አባቶች ገድል ሕብረት፣ ፍቅርና ለአንድ ዓላማ በጋራ መቆምን ሊማር እንደሚገባ አመልክቷል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የሰላም መደፍረስ ተከላክሎ የተሻለች ሀገር ለመገንባት ሁሉም በተሰማራበት ሙያ ለውጤት መስራት እንዳለበት ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም