ቀጥታ፡

ድሉን ለአንድነታችን መጠናከርና ድህነትን ለመዋጋት ማዋል ይገባናል ሲሉ ምሁራን አስገነዘቡ

አርባ ምንጭ የካቲት 23/2011 አያቶቻችን አድዋ ላይ ያስመዘገቡትን ታሪካዊ ድል አንድነታችንን ለማጠናከርና ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለመውጣት ልናውለው ይገባል ሲሉ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አመለከቱ።

የአድዋ ድል 123ኛው በዓል ዛሬ በዩኒቨርሲቲው ተከብሯል።

የዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ካሡ ጡሚሶ በበዓሉ ላይ እንደተናገሩት ድሉን አሁን ያሉብንን ችግሮች ለመወጣት መጠቀም ይገባል።

አገሪቱ ያሉባትን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታትም በአንድነት ከመቆም የተሻለ አማራጭ እንደሌለም አስረድተዋል።

''አያቶቻችን የታሪክ ግዴታቸውን ሠርተው እንዳለፉ ሁሉ፤ እኛም ድህነትን የማሸነፍ ገድላችንን መወጣት ግደታችን ነው'' ብለዋል ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስና ስነሰብ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ሙሉጌታ ደበሌ ''በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አውሮፓውያን የአፍሪካን ሀብትና የገበያ አማራጮችን እንደ ልደት ኬክ ለመቀራመት የተሻኮቱበት ነበር'' ብለዋል ፡፡

በዚህ ም በ1888 የጣልያን ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን ለማስገበር ያደረገው ሙከራም በከሽፈበት በአርበኞቹ ድባቅ መመታቱንም አስታውሰዋል።

ዛሬ ለአገር አንድነትና ብልጽግና በምናደርገው  ጥረትም  ይህንን የአይበገሬነትና የአንድነት መንፈስ ወስደን ወደ ብልጽግና መንገድ መግባት አለብን ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የጋሞ ዞን አባት አርበኞች ማህበር ፀሐፊ አቶ ጌታቸው ዓለማየሁ በአንድነት መንፈስና በመቻቻል የተገነባውን ኢትዮጵያዊነታችን ይዘን የጋራ አገራችን ለመገንባት መትጋት ይኖርብናል ሲሉ  ምክራቸውን ለግሰዋል።

በበዓሉ ላይ በምሁራን የድሉን ታሪካዊነት የሚያሳይ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም