ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቢስክሌት ቡድን ባህር ዳር ገባ

ባህር ዳር የካቲት 23/2011 የኢትዮጵያ ቢስክሌት ብሄራዊ ቡድን  በ14ኛው የአፍሪካ ቢስክሌት ሻምፒዮና ለመካፈል ዛሬ ማምሻውን ባህርዳር ገብቷል።

ብሔራዊ ቡድኑ 35 አባላት ያሉት ሲሆን ፤በከተማዋ ሲደርስም አቀባበል ተደርጎለታል።

የወንዶች ቢስክሌት ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ንጉሤ ገብረ ዮሐንስ እንደገለጹት  በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን ሻምፒዮና በውጤታማነት ለማጠናቀቅ  ተዘጋጅቷል።

ቡድኑ በተለያዩ አገሮች ባደረጋቸው ውድድሮች ያካበተውን ልምድ እንደሚጠቀምበትም አስረድተዋል።

ቡድኑ በሽሬ እንዳስላሴ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው፣እስከ ውድድሩ ባሉት ዝግጅቱን ይቀጥላል ብለዋል።

የሴቶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አቶ መሀሪ ዱሪ በበኩላቸው 16 ሴት ቢስክሌተኞች በወጣት፣ በአዋቂ ሴቶችና በሌሎችም ውድድሮች እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።ውድድሮቻቸውን በአሸናፊነት ለማጠናቀቅም ልምምዳቸውን እንደሚቀጥሉም አስረድተዋል።

ሻምፒዮናው በአገሩ መካሄዱ ውድድሩን በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥርለት የተናገረው ደግሞ የብሄራዊ ቡድኑ ተወዳዳሪ ተመስገን መብርሃቱ ነው።

ከዚህ በፊት በተካሄዱ አህጉር አቀፍ ውድድሮች በግልም ሆነ በቡድን እንዳሸነፈ ያስታወሰው ተመስገን፣አሁንም በአገሬ ድሉን ለመድገም ዝግጁ ነኝ ብሏል።

የሴቶች ቢስክሌት ብሄራዊ ቡድን ተወዳዳሪ ኤደን በቀለ በበኩሏ በግልም ሆነ በቡድን ለአገሬና ለራሴ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ተዘጋጅቻለሁ ብላለች።

በባህርዳር ኤርፖርት ሲደርሱም በተደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸውንም የቡድኑ አባላት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም