ቀጥታ፡

የአዳዲስ የስራ ዘርፎች አለመፈጠር በተመሳሳይ ስራ በመሰማራት ለኪሳራ ይዳርጋል-ነጋዴዎች

የካቲት 23/2011 በአዲስ አበባ የተጠኑ አዳዲስ የስራ ዘርፎች ተግባር ላይ ባለመዋላቸው ሰዎች በተመሳሳይ የስራ ዘርፍ በመሰማራት ለኪሳራ እየተዳረጉ መሆኑን አስተያየት ሰጪ ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡

የፌደራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በበኩሉ አዳዲስ የስራ ዘርፎች ያካተተ ስቴራተጂክ  ሰነድ እየተጠና መሆኑን አሳውቋል፡፡

ጊዮርጊስ አካባቢ ያገኘናት ወጣት ሙሉ እመቤት ተስፋዬ ከ7 አመት በፊት ወደ ልጆች  ልብስ ንግድ ስትገባ  በአካባቢው 2 ብቻ እንደነበሩ ታስታውሳለች፡፡

አሁን ላይ 15 መድረሳቸውንና የተመሳሳይ ስራዎች መብዛት ተፅእኖው ገበያ ማጣት መሆኑን ገልፃ  ከሽያጩ የሚገኘው ገቢ የቤት ክራይ የማይሸፍንበት ሁኔታም እንዳለ ተናግራለች፡፡

ነጋዴው ተመሳሳይ ስራ ላይ እንኳን ቢሰማራ በመናበብ አንዱጋ ያለውን እቃ አንዱ ባይዘው  ያለችው ወጣቷ  “ፉክክሩ ግን ሁሉንም ይጎዳል  አንድ አይነት የዋጋ ተመንም መያዝ ይገባል” ብላለች፡፡

የንግድ ስራው በእውቀት የተደገፈ አለመሆኑ ብዙዎችን እየጎዳ መሆኑን የምትናገረው ሙሉ እመቤት 6 ወር ኪራይ ቀድመው ከፍለው በስራ ውስጥ አንድ ወር እንኳን መቆየት ያልቻሉ ሰዎች መኖራቸውን ተናግራለች፡፡

አማራጭ ስራዎችን ከመመልከት ይልቅ አንዱየሚሰራውን ስራ ሌላውም ሳያጠና መድገሙ ለኪሳራ የሚዳርግ መሆኑን ነው የገለፀችው፡፡

አሁን ላይ እየተዘወተረ የመጣው የቡና ማፍላት ንግድ ግን ሰዎች ሳይከስሩ እየሰሩበት መሆኑን መታዘቧን ጠቅሳለች፡፡

መንግስት በንግድ ክህሎት ስልጠና ላይ በስፋት መስራት እንዳለበትም ሳትጠቅስ አላለፈችም፡፡

ሌላው ወጣት ሙስጠፋ ሙሻቃ እንዳለው የንግድ ስራን የጀመረው በአካባቢው ሲሰራ ባየው የመጽሀፍ  ሽያጭ ነው ፤አላዋጣ ሲለውም አትክልት ቤት ከዚያም የስራ ቦታውን ያከራየበትን ሁኔታ ያስታውሳል፡፡

ሆኖም እንደገና የአካባቢውን ሁኔታ በማጥናት ብድር ወስዶ የቤት እቃዎችን መሸጥ መጀመሩን ያወሳል፡፡

ንግድ  ላይ ለመቆየት ፍላጎትና ቢዝነሱን ማጥናት ይቀድማል የሚለው ሙሰጠፋ እንዱ የሰራውን ደግሞ መስራት “ገደል መግባት ነው ከልምድ አይቼዋለሁ” ብሏል፡፡

ወጣቱ እንዳለው ስራን በራስ ዝንባሌ ሞክሮ ማየት ጥሩ ነው ፣በአካባቢው ላይ ምን ይሄዳል የሚለውን ማጥናትም ይገባል ፡፡

6 ኪሎ አካባቢ ያገኘነው  ወጣት ኤርሚያስ  መርሻ  ወደ አዲስ አበባ  ሲመጣ  ከጫማ ማፅዳት ጀምሮ  የልብስ ጥገና እና ጌጣጌጦችን በእጁ ይሰራ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

“አካል ጉደተኛ ብሆንም በአንድ እግሬ እየታገዝኩ  የልብስ ጥገናም ሰርቻለሁ” የሚለው ኤርሚያስ  አሁን ላይ በአትክልት ንግድ ላይ መሰማራቱን ጠቁሟል፡፡

በመንግስት በኩል ለስራ ፈጣሪዎች  በቴክኒክና ሙያ  ኮሌጆች በኩል የሚሰጠው ስልጠና በአሰልጣኞች ምርጫና በውስን ዘርፎች ብቻ መሆኑ ፈጠራን የማያበለፅግና በልምድ የተገኘ ክህሎትን የማያበረታታ ነው ብሏል፤ ይህም ለስራ ድግግሞሽ አንዱ መንስኤ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

የፌደራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ አሰፋ ፈረደ አንዳሉት በ2003 የተቀረፀው የጥቃቅንና አነስተኛ ስትራተጂ በአምስት ዋነኛ ዘርፎችና በመንግስት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የስራ እድል መፍጠርን አልሞ የተቀረፀ ነው ፡፡

ማኑፋክቸሪንግ፣ የኮንስትራክሽን፣የንግድ፣ አገልግሎትና  የከተማ ግብርና ዘርፍ ዋነኛ መሆናቸውን ጠቅሰው  አሁን ላይ የአለም ነባራዊ ሁኔታና  ኢኮኖሚው የሚያመነጫቸውን ዘርፎች ለመጠቀም የሚያስችል የስትራተጂ ክለሳ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ አዳዲስ የስራ ዘርፎች ላይ በቂ ስልጠና ሰጥቶ ወደ ስራ ማስገባት ላይ ውስንነቶች አሉ የሚሉት አቶ አሰፋ “ከተቀረፁት የስራ ዘርፎች ውጪ አደራጅተን ማሰማራት አንችልም” መባሉ ስራፈጣሪዎችን ላይ ቅሬታ መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡

በተለይ ወጣቶችን በሙሉ አቅም ወደ ስራ ለማስገባት የብድር አቅርቦቱ ከፍላጎቱ አለመጣጣሙ፣የብድር ዋስትና መጠየቅ፣የመስሪያና የመሸጫ ቦታ በቂ አለመሆንና የመሰረት ልማት አለመሟላት ፣የስልጠና ተደራሽነትና ጥራትም የስራ እድል ፈጠራው ተግዳሮት መሆኑን አንስተዋል፡፡

በቀጣይ በሚካሄዱ ምክክሮች ዘርፉን የሚፈታተኑ ማነቆዎች  በሃገር አቀፍ ደረጃ ተለይተው የመፍትሄ አቅጣጫ ይቀመጥላቸዋል ብለዋል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ፋሲል ጣሰው  በሰጡት አስተያየት ዜጎች ስራ ፈጣሪና አዳዲስ ሃሳቦችን የሚያመነጩ እንዲሆኑ ከትምህርት ቤት ጀምሮ መሰራት ይገባል፡፡

ጅምር ስራዎች  ቢኖሩም  ወጥነት ይጎላቸዋል ያሉት አቶ ፋሲል በሃገር አቀፍ ደረጃ መደላደል አልተጣለም፣ የትምህርት ማስተማሪያ መፅሃፎቻችን ሳይቀር የውጪ ሃገራት ተሞክሮዎች መሆናቸው የራሳችንን ችግር በራሳችን ለመፍታት አላስቻሉንም ብለዋል፡፡

ቴክኖሎጂዎችን ለማላመድ ብቻ ትኩረት መሰጠት እንደሌለበት ገልፀው በራስ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት  መበረታታት አለበት፤ ሃገሪቱ የምታስገባቸው ኢንቨስተሮችም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሃገር ውስጥ የሚያስገቡ መሆን እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም