በሀገር አቀፉ የባህል ስፖርቶች ውድድር የአማራ ክልል በአጠቃላይ አሸናፊ ሆነ

68

አምቦ የካቲት 23/2011 በአምቦ ከተማ ለስምንት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 16ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር በአጠቃላይ በአማራ ክልል አሸናፊነት ዛሬ ተጠናቀቀ፡፡

በውድድሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃዎችን አግኝተዋል።

በዘጠኝ ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች መካከል በ12 የስፖርት ዓይነቶች በተካሄደው ውድድር 550 ስፖርተኞች ተሳትፈዋል ።

የአማራ ክልል በሁለቱም ጾታዎች በተደረጉ ውድድሮች 68 ነጥብ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 57 ነጥብ እና የኦሮሚያ ክልል ደግሞ 44 ነጥብ በማምጣት ውድድሩን አጠናቀዋል፡፡  

በዚህም  አማራ  13 ፣ አዲስ አበባ  8  እና ኦሮሚያ  5 ዋንጫዎችን በማግኘት እንደቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ወጥተዋል፡፡

በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፀባይ ዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።

ለውድድሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

" የባህል ስፖርት ተሳትፏችን ለሰላምና ለአንድነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ ከየካቲት 16/2011 ዓ.ም. ጀምሮ ውድድሩ ሰካሄድ ቆይቶ ቆይቶ ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡

በውድድሩ ከተካሄዱ ባህላዊ ጨዋታዎች መካከል ገበጣ፣ ገና፣ የፈረስ   ጉግስ፣ ቀስት፣ ኩርቦና ትግል ይገኙበታል፡፡

የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ሰለሞን አስፋው ለአሸናፊ ክልሎች ዋንጫና ሽልማቶችን ከሰጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር " የስፖርት ውድድሩ  ዓላማ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ቱባ ባህሎቻቸውን ለማስተዋወቅና ልምድ ለመለዋወጥ ነው "ብለዋል፡፡

የአምቦ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎችም ጨዋነት በተላበሰ ሁኔታ  ስፖርተኞችን  በማስተናገድና በማበረታታ ላበረከቱት አስተዋጽኦም አመስግነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም