ቀጥታ፡

ለሥራ ወደ ውጭ የሚወጡ ዜጎች የተመቻቸላቸውን ህጋዊ አሰራር እንዲከተሉ ተጠየቀ

አዲስ አበባ የካቲት 23/2011 ከኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ለሥራ  የሚሄዱ ዜጎች ከህገ-ወጥ ስደት ይልቅ መንግስት ያዘጋጀላቸውን ህጋዊ አሰራር መከተል እንዳለባቸው የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ።

መንግስት ወደ ውጭ ለሥራ  የሚሄዱ ዜጎች ሰብዓዊ ክብራቸውንና ደህንነታቸው ተጠበቆ መስራት እንዲችሉ ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጋር የጋራ ስምምነት ሰነድ አዘጋጅቷል። 

ከዚህም ሌላ ዜጎች በህገ ወጥ ስደት የሚያጋጥማቸውን አደጋ ለመከላከልና በሥራ  ላይ የሚደርሰባቸውን በደል ለማስቀረት ከተለያዩ አገራት ጋር መስራት የሚቻልበትን ስርዓት የሚመራ የውጭ አገር የስራ ስምሪት አዋጅ ወጥቷል።

የዛሬ ሶስት ዓመት ግድም የወጣው አዋጅ  ከኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ አረብ አገራት ለሥራ  የሚሄዱ ዜጎች ሰብዓዊ ክብራቸው፣ ደህንነታቸውና መብታቸው ተከብሮ በውጭ የመስራት ፍላጎታቸውን ለማሟላት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

ህገ ወጥ ስደት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራት የሰዎች ፍላጎት እስካለ ድረስ የማይቀር ቢሆንም መጠኑን ግን በመንግስታት ጥብቅ ቁጥጥር መቀነስ ይቻላል።

ዓለም አቀፉ የስደት ድርጅት እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2018 ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ከዓለም ህዝብ 3 ነጥብ 3 በመቶ ወይም 244 ሚሊዬን የሚጠጉ ዜጎች ህይወታቸውን በስደት ይገፋሉ።

በኢትዮጵያ ከአገሪቱ ህዝብ ብዛት ወደ አንድ በመቶ የሚጠጋ ስደተኛ ቢኖርም በየዓመቱ ከኢትዮጵያ ወደ ሩቅ ምስራቅ እና የተለያዩ አገሮች በህገ ወጥ መንገድ የሚወጣው ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል። 

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ይርጋለም ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የውጭ አገር የስራ ስምሪት አዋጅ የዜጎችን ህገ-ወጥ ስደት ለመከላከል የሚያስችል ነው።

በመሆኑም ዜጎች ህገ-ወጥ ስደትን ወደጎን በመተው ደህንነታቸው ተጠብቆላቸው መስራት የሚያስችላቸውን ህጋዊ የአሰራር ስርዓት መከተል አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ።

የዜጎችን ደህንነት ለመከታተል ሲባል ወደተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ለስራ መሄድ የሚችሉት ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እውቅና ሲያገኙ ብቻ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ወደ ውጭ አገር ለስራ ከሚልኳቸው ሰራተኞች ክፍያ መቀበል በአዋጁ የተከለከለ በመሆኑ ሰራተኞች መብታቸውን መጠቀም አለባቸው ሲሉም አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ የውጭ አገር የስራ ስምሪት አዋጅ ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገሮች የሚሄዱ ዜጎች መነሻ ወርሃዊ ደመወዝ ከ850 ወደ አንድ ሺህ ሪያድ ከፍ መደረጉን ገልጸዋል።

በቀጣይም የአዋጁን አተገባበር በተመለከተ  በየስድስት ወሩ ከአገሮቹ ጋር በሚደረግ ምክክር ማሻሻያ ይደረጋል ብለዋል።

በውጭ ሥራ የሚሰማሩ ዜጎች ቤተሰቦች ያሉበትን ቦታ ማወቅ ቢፈልጉ በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበት እንዲሁም ለሰራተኞች የጤና ኢንሹራንስ እንዲገባ የሚያስገደድ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ሰራተኞቹ ወደ ስራ ከመግባታቸው በፊት ስለሚሄዱበት ስራ መንግስት በነጻ አሰልጥኖ የሙያ ብቃት ምዘና እንዲወስድ ይደረጋል ነው ያሉት አቶ አሰፋ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም