የአድዋ ጦርነት የተመራበት ፍልስፍና ኢትዮጵያ ለዓለም ታላቅነቷን ያስመሰከረችበት ነበር - የታሪክ አዋቂዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ጦርነት የተመራበት ፍልስፍና ኢትዮጵያ ለዓለም ታላቅነቷን ያስመሰከረችበት ነበር - የታሪክ አዋቂዎች
አዲስ አበባ የካቲት 23/2011 ከአድዋ ድል ባሻገር ጦርነቱ የተመራበት ፍልስፍና ኢትዮጵያ በወቅቱ ለዓለም ታላቅነቷን ያስመሰከረችበት ነበር ሲሉ የታሪክ አዋቂዎች ተናገሩ።
ጊዜው አውሮጳዊያን አፍሪካን ለመቀራመት የቋመጡበት ነበር። የቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ ቆማ የነበረችው ኢጣልያም ኢትዮጵያን የራሷ ለማድረግ ያግዘኛል የምትለውን ማድረግ ጀመረች።
የኢጣልያ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር የተስማማበትን 20 አንቀጾች ያሉት የውጫሌ ውል 17ኛ አንቀጽ ትርጉም በማዛባት ኢትዮጵያን እንደፈለገ ለማድረግ ተመኘ።
ይህን የተረዱት ንጉስ ምኒልክ ስምምነቱን አለመቀበላቸውን ለአውሮጳ አገራት በደብዳቤ አሳወቁ። ኢጣልያም ጦሯን ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት ጀመረች፡፡
አጤ ምኒልክ ሁኔታው ቢያስቆጣቸውም ጦርነት እንዲቀሰቀስ ፍላጎት አልነበራቸውም። ጦርነቱ አይቀሬ ሲሆን ግን በስተመጨረሻ የክተት አዋጅ ለህዝባቸው አስተላለፉ። በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሠራዊትም መሪዎቹን አጅቦ ወደ ጦርነቱ ተጓዘ።
የዛሬ 123 ዓመት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ኢትዮጵያዊያን ነጻነታቸውን አወጁ፤ የጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነውን የአድዋ ድል አስመዘገቡ።
የአድዋ ድል አፍሪካዊያን አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ መሰረት የጣለ መሆኑን የሚናገሩት ታሪክ አዋቂዎች ጦርነቱ የተመራበትን ፍልስፍና እና በወቅቱ የነበረውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ያደንቃሉ።
ንጉስ አጤ ምኒልክ በአሁኑ ወቅት ዓለም የምትመራባቸውን ህጎችን ቀድመው በመተግበርና እስከ አራት ሺህ የሚሆኑትን የኢጣልያ ምርኮኞች በሰብአዊነት በመያዝ ፈር-ቀዳጅ መሆናቸውን በመግለጽ ጭምር።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንደገለጹት ንጉስ አጤ ምኒልክበዚያን ጊዜ በነበረ አስተሳሰብ ጉልበት አለኝ ብሎ አገር ሊወር የመጣን ጦር ሲማርኩት መሟላት ያለባቸውን ምግብ፣ መኝታ፣ መጠለያ አቅርበው በሰብዓዊነት መያዝና ማቆየት የሚያስገርም ነው ብለዋል
የአንድ ኢጣልያዊ ምርኮኛ ወታደር እናት ለልጇ ደብዳቤ ጻፈች። አጤ ምኒልክም እስረኛውን አስመጥተው ደብዳቤው እፊታቸው እንዲነበብ አደረጉ።
ደብዳቤውን ካዳመጡ በኋላም፣ አዝነውና አልቅሰው "ሂድ በነፃ አሰናብቼሃለሁ፤ የእናትህ እንባ አማለደህ" ብለው አሥመራ ድረስ በበቅሎ እንደሸኙት የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
"የንጉሱ ይህን መሰሉ ድርጊት የአስተሳሰባቸውን ምጡቅነት የሚያሳይና ከባህሪያቸው ጋር የሚያያዝ ነው" ሲሉ ነው ዶክተር ሳሙኤል የሚገልጹት።
"የምኒልክን ጥልቅ የሆነ ባህርይ ስንረዳ ለብዙ ነገሮች የነበራቸው ለየት ያለ አስተሳሰብ አሁን ቴክኖሎጂ ከመቀበል፤ ስልክ የሰይጣን ስራ ነው ሲባሉ በኃይማኖት በጣም ጫና በነበረበት ጊዜ እውነትም የሰይጣን ስራ ሊሆን ይችላል ብለው ማመን በነበረባቸው ጊዜ አይደለም ብለው አምነው ስልክን ሲቀበሉ፣ መኪናን ሲቀበሉ፣ አውሮፕላንን ሲቀበሉ ብዙ ነገሮችን ሲቀበሉ ይሄ ነገር የምኒልክን በሳልበት ነው የሚያሳየን በወቅቱ የነበራቸውን ነገሮችን የመረዳት ነገር ነው የሚያሳየው ሰብዓዊነቱን ከዚሁ ጋር የሚያያዝ ነው"። ሲሉ ዶክተር ሳሙሄል አስረድተዋል
በወቅቱ በአገሪቱ የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩም በውጭ ወራሪ ኃይል ላለመደፈር ምኒልክ ህዝቡን በአንድነት ያስተባበሩበትና አንድነት ኃይል መሆኑን ለዓለም ያሳዩበት ድል ሌላው በታሪክ ባለሙያዎች የሚደነቅ ተግባር ነው።
የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር እውነቱ በላቸው እንደሚሉት አድዋ የተመራበት ፍልስፍና የአገር አንድነትን ማዕከል ያደረገ የኢትዮጵያዊያን የስነ-ልቦና ማሳያ ነው።
"ዘመቻው በዋናነት በኋላም ውጤቱ የአገር አንድነት መሰረት ያደረገ ተብሎ ነው የሚታየው የአድዋ ጦርነት በዋነኛነት የኢትዮጵያዊያንን ስነ-ልቦና ያስመሰከረ ነው። አንደኛ ከጦርነቱ በኋላ አሸንፈናል የሚል የእኩልነት፤ አንዳንዶች እንደሚሉትም የበላይነት ስሜት፤ ሁለተኛው ጦርነት ውስጥ መግባት በራሱ አላንስም ኢትዮጵያዊያን ድል እናደርጋለን ብለው ከመቶ ሺህ በላይ ሰራዊት መሄዱ የስነ-ልቦና ማሳያ ነው ፍልስፍናው በራሱ። የአድዋ ጦርነት አልሸነፍ ባይነትን በተግባር ያሳየ ተብሎ ነው የሚታወቀው"።ሲልየታሪክ መምህር እውነቱ በላቸው አስረድቷል
ይሁንና ይህ የአንድነትና የአሸናፊነት መንፈስ አገሪቱን ወደኋላ በሚጎትቱት ድህነት፣ ኋላቀርነትና ጎጠኝነትን የመሳሰሉ ወቅታዊ የአገሪቱ ጠላቶችን ድል ለማድረግ በአሁኑ ትውልድ አልተደገመም ባይ ናቸው።
ይህም ታሪክን በአግባቡ ባለማስተማርና ለትውልዱ አገር በቀል ዕውቀቶችን ባለማውረስ የመጣ ነው ይላሉ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ዶክተር አልማው ተክሌ።
"ክፍተት አለ፤ ትውልዱ ላይ አልሰራንም። ከአድዋ በኋላ በሶሻሊዝም ወደ ራሺያ ነው ይዘነው የሄድነው፤ አሁን ደግሞ ወደ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወደ አልቤኒያ ነው ይዘነው የሄድነው፡፡ አገር ውስጥ ለትውልዱ የሚማረው ነገር አልሰጠነውም፤ ውጪን ነው ያሳየነው እንጂ አገሩን አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው በአውራ ጣቱ ውጪን ለማየት ነው የሚቆመው አገር በቀል ባህል፣ አገር በቀል እውቀት፣ ስለታሪክ አልሰበክነውም ምንም ያስተማርነው ነገር የለም ባዶ እጁን ያለ ትውልድ ነው። እና ይሄ ትውልድ ሊወቀስ አይገባም ፡፡እኛ ነን ጥፋተኞች ያስተላለፍልነት አገር በቀል ነገር የለም"። ሲሉ ተናግረዋል
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ደግሞ ትውልዱ መስዋዕትነት ከፍሎም ቢሆን ነገሮችን መቀየርና ለቀጣዩ የተሻለች ኢትዮጵያን መፍጠር ይኖርበታል ነው የሚሉት።
"የትኞቹም ሰለጠኑ የሚባሉ አገራት እኮ በአንድ ወቅት ሁለት ሶስት ጀኔሬሽን ላይ ጫና ፈጥረው፤ ያ ጀነሬሽን ተጎድቶ አገሪቱ ግን መሰረት ጥላ ጥሪት አግኝታ ከዛ በኋላ ነው እንጂ አደጉ የሚባሉት በኢንዱስትሪ በለጸጉ የሚባሉት 'ጫማ በልተው ነው ይባላል' የአገላለጽ ጉዳይ ቢሆንም በባዶ እግራቸው ሄደው ነው ማለት ነው፡፡ ዛሬ የተስተካከለ የኑሮ ደረጃ ላይ አብዛኛው ህብረተሰባቸው እንዲኖር አድርገዋል እና ይሄንን ለማድረግ እኔም ሁልጊዜ የማስበው በተወሰነ ደረጃ ሊጎዳ የሚገባው ትውልድ አለ፤ ያ ትውልድ እኛ ብንሆን በታሪክ ተጠቃሚ ነው የምንሆነው። በልጆቻችን የምንመሰገን ነው የምንሆነው፤ የምናወርሳቸው ጥሩ ነገር ነው"። ብለዋል ዶክተር ሳሙሄል ክፍሌ
በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ነገሮችን እያጋጋሉ በህዝቦች ዘንድ መቃቃር መፍጠርን በመተው በአንድነት መሰረታዊ ችግሮች ላይ በማተኮር ዳግም ባለድል መሆን ይቻላል የሚለው የታሪክ አዋቂዎቹ አስተያየት ነው።