የትግራይ ክልል ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ 250 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደርጋለሁ አለ - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ክልል ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ 250 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደርጋለሁ አለ
አድዋ የካቲት 23/2011 የትግራይ ክልል መንግስት ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ 250 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያደርግ የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ተናገሩ።
ምክትል ርዕሰ-መስተዳድሩ እንዳሉት "የአድዋ አንፀባራቂ ድል አገራዊ ፋይዳ ያለው፤ ለውጭ ኃይል የማንንበረከክ፤ ለነፃነት ወደኋላ የማንል በማንነት ሳንለያይ ሊገመት የማይችል ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ማሳያ ነው"።
የአድዋ ታሪክ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን በአሁኑ ወቅት "የውጭ ተፅዕኖ በተዘዋዋሪ ሁኔታ ስለሚፈፀም አገሪቱን ከማንኛውም የውጭ ጣልቃ ገብነት መከላከል ይገባል" ብለዋል።
አድዋ በተገቢው ሁኔታ መጠናትና መጠበቅ ይገባዋል በማለትም የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግም መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በተለየ የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ለመገንባት እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልፀው ዩኒቨርሲቲው በተለይም አፍሪካዊያን ምርምር የሚያደርጉበት ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲውን እውን ለማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መተባበር እንዳለበት መክረው የትግራይ ክልል ለዩኒቨርሲቲው ግንባታ 250 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑም ይፋ አድርገዋል።
የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምን ጨምሮ ሌሎች ከድሉ ጋር ተያያዥ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ክልሉ ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።