በባሌ ዞን ኩፍኝን ለመከላከል ክትባት በዘመቻ መስጠት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ዞን ኩፍኝን ለመከላከል ክትባት በዘመቻ መስጠት ተጀመረ
ጎባ የካቲት 23/2011 በባሌ ዞን ህጻናትና ታዳጊዎችን ከኩፍኝ በሽታ ለመከላከል ከትናንት አንስቶ ክትባት በዘመቻ መስጠት መጀመሩን የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ዶክተር ሀምዛ ሱልጣን ለኢዜአ እንደገለጹት ክትባቱ ለአራት ቀናት ይሰጣል።
በ18 ወራዳዎች በሚገኙ ጤና ተቋማትና ቤት ለቤት በሚሰጠው የክትባት ዘመቻ ላይ ከ2 ሺህ የሚበልጡ የጤና ባለሙያዎች፣ተቆጣጣሪዎችና መንገድ መሪዎች ተሰማርተዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ ክትባቱ የሚሰጠው በዞኑ በአስር ወረዳዎች ውስጥ የተከሰተውን የኩፍኝ በሽታ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዘመት ለመቆጣጠር ነው።
በክትባቱ ዕድሜያቸው ከስድስት ወር እስከ 15 ዓመት ለሆናቸው ከ800 ሺህ ለሚበልጡ ህጻናትና ታዳጊዎችን ለመሸፈን መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለክትባት ዘመቻው የሚያስፈልገው ቁሳቁስና የሰው ኃይል በሁሉም ወረዳዎች መሟላታቸውን ያመለከቱት ዶክተር ሀምዛ ህብረተሰቡም ልጆቹን በወቅቱ በማስከተብ በሽታው እንዳይስፋፋ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡
"ከክትባቱ አገልግሎት ጎን ለጎን በበሽታው የተያዙ ህጻናትን በመለየት ወደ ጤና ተቋማት በማምጣት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋልም "ብለዋል፡፡
በዞኑ የክትባት ዘመቻው እንዲሳካ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት የመድኃኒትና ሌሎችንም የግብአት ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የመዳ ወላቡ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ ሌይላ በከር በሰጡት አስተያየተ ወረርሽኙን ለመከላከል ከክትባት አቅርቦቱ በተጓዳኝ በማህበረሰቡ ግንዛቤ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
መንግስት በየጊዜው ለልጆቻቸው በነፃ የሚሰጠው የክትባት አገልግሎት ጤንነታቸው እንዲጠበቅ ማስቻሉን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ሙንተሃ ሁሴን ናቸው፡፡
የኩፍኝ በሽታ በሳልና በሚያስነጥስ ወቅት ከአፍና ከአፍንጫ በሚወጣው እርጥበት አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው በትንፋሽ የሚተላለፍ ነው፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በባሌ ዞን ከሚኖረው አንድ ሚሊዮን 800 ሺህ ህዝብ ውስጥ 16 ነጥብ 4 በመቶው ህፃናት ናቸው።