የኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ትርክት በአድዋ የድል እሳቤ ውስጥ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ትርክት በአድዋ የድል እሳቤ ውስጥ

ሃብታሙ አክሊሉ(ኢዜአ)
“ኢትዮጵያዊነት” እኛ ባለቤቶቹ የምንኮራበት ብቻም ሳይሆን ከድንበር ወዲያ ማዶ ላሉ ወንድሞቻችን ከቅኝ ግዛት የባርነት ቀንበር መላቀቅ ምክንያታቸው፣ ከበታችነት ስሜት ወደ ላይኛው የስብዕና መንበር የተሸጋገሩበት አስተሳሰብ ነው። “ኢትዮጵያዊነት’’ በአንዳንድ ወገኖች ተዛብቶ እንደሚቀርበው አይነት ሳይሆን ምሉዕነት ያለውና በአለም አቀፍ ደረጃ ግዙፍ የአሸናፊነት ተምሳሌትም ነው። በዚህ የአሸናፊነት ምሳሌ ውስጥ ደግሞ ጥንት አባቶቻችን በባዶ እግር በመጓዝ፣ ረሃብና ውሃጥም ሳይበግራቸው ወራሪውን የነጭ ተስፋፊ ሃይል ድል የነሱበት የአድዋ ድል በአል ትልቁን ስፍራ ይይዛል። ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊነትን ከአሸናፊነት፤ የማሸነፍ ስነ ልቦናን ደግሞ ከአድዋ ተራሮች ገድል ይቀዳል ማለታችን።
ጥንት አባቶቻችን እንደ አንድ መክረው፣ እንደ አንድ ወስነው፣ በአንድ ወኔና ተነሳሽነት እስከ አፍንጫው ታጥቆ የመጣን ወራሪ ሃይል መመከት የቻሉበት የአድዋ ድል በአል እንሆ 123ኛው ላይ ደረሰ። እዚህ ግባ በማይባል የጦር መሳሪያ ነገር ግን የህብረት ክንድ ባጠነከረው ወኔ አባት አያቶቻችን ያስመዘገቡት ድል በአስገራሚነቱ እስካሁንም አነጋጋሪ እንደሆነ ነው። የዛሬ 123 አመት የተፈፀመው የጦር ሜዳ ገድልን በወቅቱ የነበሩ ታዋቂ መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር ብዙ ብለውለታል። በያመቱም በሚካሄደው የድል በአል አከባበር ላይ የአፍሪካም ሆነ አለም አቀፍ ሚዲያው ስለ አድዋ ፅፈውና ተናግረው ሊጨርሱ አልቻሉም። በተለያዩ ጊዜያትም አድዋን እያነሱ ለህዝባቸው አልበገር ባይነትንና አሸናፊነትን እያስተማሩበት ይገኛል። የሃገር መሪዎች ሳይቀሩ ስለ አድዋ ዘመን ተሻጋሪ አስተያየቶችን ሰጥተውበታል። በተለያዩ ጊዜያት የትኞቹ መገናኛ ብዙሃን ስለ አድዋ ምን አሉ የሚለውን ቀጥለን እንመልከት።
የአድዋ ድል የአለማችንን ታሪክና ፖለቲካ ከላይ ወደ ታች እንዲገለባበጥ ያደረገ የኢትዮጵያውያን ብሎም የአፍሪካውያን ድል ነው ሲል ስለ አድዋ ባወጣው ዘገባ ላይ ያነሳው ኦሪጅንስ ዶት ኮም አውሮፓውያን በአፍሪካውያን ላይ ይዘውት የቆዩትን አመለካከት የቀየረ እንደነበርም አስታውሷል።
የአድዋ ጦርነት ዝም ብሎ ከተራ ትርክት የሚመደብ ጦርነትም አይደለም በማለት ሃሳቡን ያጠናከረው የድረ ገፁ ፀሃፊ በአንድ ወቅት የአድዋ ጦርነትን አስመልክቶ ብዕሩን ያነሳውን ሬይሞንድ ጆናስ የተባለን ፀሃፊ ሃሳብ ይጋራል። ሬይሞንድ ጆናስ የጦርነቱን የኋላ ዳራ፣ጦርነቱንና ከጦርነቱ በኋላ የነበሩ ክስተቶችን ግልፅ አድርጎ በብዕሩ የከተበ የታሪክ ፀሃፊ ነው። ፀሃፊው የአድዋን ጦርነትና ከዚያም በኋላ የተገኘው ድል አመጣ ባላቸው ሶስት ጉዳዮች ላይ ተመርኩዞ ይገልፃቸዋል።
እንደ ፀሃፊው አድዋ የቅኝ ገዥነት አስተሳሰብን የገታ የጣሊያን ቅኝ ገዥን ጉልበት በአርበኝነት ተጋድሎ ያሽመደመደ ነው። የአድዋ ድል የወራሪው የጣሊያን ጦርን ቅስም የሰበረ በወቅቱ የነበረውን የጣሊያን ገዥ ሃይል በራሱ ተማሪዎች ‘’ቪቫ ምኒሊክ” እንዲሉ ያስገደደ ድል ነው። በወቅቱ የአፍሪካን አህጉር ይዞ ሲበዘብዝ ለነበረው የቅኝ ወራሪ ሃይል አድዋ ትልቅ ትምህርትን ያስተላለፈ መሆኑንም ፀሃፊው እንደ መጀመሪያ ጉዳይ ያነሳል።
የጦር ጀግኖች ድልን ባጣጣሙበት ቅፅበት ሰዋዊ አስተሳሰባቸውን ያጡና ሌሎች ያልተገቡ ድርጊቶችን ሲፈፅሙ ማየት የተለመደ በሆነባት አለም አጼ ምኒልክ ለምርኮኞቻቸው ያሳዩትን ርህራሄ ፀሃፊው በአድናቆት ከገለፃቸው ጉዳዮች በሁለተኝነት ይጠቀሳል። የባለቤታቸውን የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ጠንካራ ድጋፍ ወደ ተግባር ማምጣቱ ለውጤታማነት እንዳበቃቸው ያነሳው ሬይሞንድ ጆናስ ይህም የአጼ ምኒልክን ብልህነት እንደሚያሳይ መስክሯል።የአጼ ምንልክና እቴጌ ጣይቱ የጀግንነት ተግባር ስፔንን አንድ ካደረጉት ባልና ሚስት ፈርዲናንድና ኢዛቤላ ጋር በማገናኘት ፀሃፊው ገልፆታል። ህዝቡን ለአንድ አላማ በጠንካራ ተነሳሽነት እንዲተም በማድረግ ለአለም ህዝብ አስገራሚ ድል አድራጊነትን ያሳዩ መሪ መሆናቸውም ፀሃፊው የምኒልክን ብልህነት ከገለፀባቸው ጉዳዮች ይጠቀሳል።
ሌላውና ፀሃፊው በሶስተኛነት ያነሳው ጉዳይ የአድዋ ድል ለአፍሪካውያን ብሎም ለአፍሪካ አሜሪካውያን የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ምልክት መሆኑን ነው። የአድዋ ድል አጼ ምኒልክ በትረ ስልጣናቸውን አጠናክረው የሃገራቸውን ነፃነት እንዲያስከብሩ ያደረጋቸው ሲሆን ለፓን አፍሪካን ራዕይ አቀንቃኞች ደግሞ በተምሳሌትነቱ የሚጠቀስ ነው። ለዚህም ይመስላል እኤአ በ1904 የሃይቲው የፓን አፍሪካ ባለ ራዕይ ቤኒቶ ሲልቪያን እንደ ሌላኛዋ ሃገሩ ወደሚቆጥራት ኢትዮጵያ መምጣቱ። ሃይቲ በ18ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ የመጀመሪያዋ የተሳካ የጥቁሮች አብዮት የተካሄደባት ሃገር መሆኗን ፀሃፊው ሳይዘነጋ ማለት ነው። የአድዋ ድል በአለም ታሪክ ውስጥ ነጮች ስለ ጥቁሮች እንዲሁም ጥቁሮች ስለ ነጮች ከድሉ በፊት የነበራቸውን አመለካከት የቀየረ ትልቁ የለውጥ መዘውር ነው፤ ሲልም ድረ ገፁ ምስክርነቱን ሰጥቶታል።
አፍሪካ ከአድዋ ድል ልትወስዳቸው የሚገቡ ትምህርቶች በርካታ ናቸው ሲል ስለ አድዋ ድል ምስክርነቱን የሚሰጠው የሩዋንዳው ኒው አፍሪካን ጋዜጣ አጼ ምኒልክ በሃገር ውስጥ የነበረባቸውን ልዩነት ትተው በወቅቱ በየራሳቸው የጦር ሃይል የነበራቸውን የየአካባቢ ገዚዎች በማስተባበር አንድ መቶ ሺ ሰራዊት ሃገሩን ከወራሪ ጠላት እንዲታደጋት ማስደረጋቸውን እንደ አንዱ ያነሳል።
ሌላኛው ደግሞ የአፍሪካ ሃገራት የውል ስምምነት (contract agreement) ሲገቡ መውሰድ የሚገባቸውን ጥንቃቄ ለአድዋ ጦርነት በመንስኤነት የተጠቀሰው የውጫሌ ውል ሂደት ትልቅ ትምህርት ሊሆናቸው እንደሚችል ኒው አፍሪካን ጠቅሷል። ከቅኝ አገዛዝ ነፃ መውጣት በኋላ አፍሪካውያን ከምዕራባውያን ጋር በሚገቡት ጥንቃቄ የጎደለው ውል ሳቢያ የአፍሪካን ሃብት መቀራመቱን የተለመደ አድርገውት እንደቆዩ ዋቢ አድርጓል።
የአፍሪካን ታሪክ ለመረዳት የአድዋን ጦርነት ታሪክ መገንዘብን ይጠይቃል ያለው ኳርትዝ አፍሪካ በጦርነቱ በሁሉም ሁኔታ የኢትዮጵያውያን አሸናፊነት የታየበት እንደነበር እማኝነቱን ሰጥቷል።ለዚህም ዘ ኒውዮርክ ታይምስ በማርች 2 ቀን 1896 ኢትዮጵያውያን በጣሊያናውያን ላይ የፈፀሙትን ታላቅ የጀግንነት ተግባር በሚያወሳውና“Abyssinians defeat Italians: Both wings of Baratieri’s army enveloped in energetic attack.” በሚል ርዕስ ያሰራጨውን ዘገባ በአስረጂነት ተጠቅሞበታል። ሽንፈቱን የተከናነበው የኢጣሊያ ወራሪ ሃይል 3ሺ የጦር ሃይል አባላቱን ሲያጣ 60 መሳሪያዎችን ጨምሮ በሁሉም የጦር ክፍሉ ላይ ከባድ ኪሳራ እንደደረሰበት ኒውዮርክ ታይምስ በቀጣይ እትሙ ላይ ይዞት ወጥቷል።የኢትዮጵያኑ የጦር ሜዳ ውሎ ስኬትና ጀግንነት በበርካታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በስፋት ተዘግቦ እንደነበርም የታሪክ ድርሳናት ከትበውት ይገኛል።
የኢትዮጵያውያን ድል ቅኝ ገዢዎች በአፍሪካ ላይ የነበራቸውን እሳቤ ከመሰረቱ የቀየረ ከመሆኑም ባለፈ ታላቅ የኋላ ዘመን ታሪካዊና ፖለቲካዊ ክስተቶች እንዲፈጠሩም ያደረገ ነበር። አፍሪካውያን በፀረ ቅኝ አገዛዝ ተጋድሎ ውስጥ በቅኝ ገዢዎቻቸው ላይ ስኬታማ ውጤት ሊያስመዘግቡ እንደሚችሉ የተነበየ ብሎም ያሳየ ድል ነው ሲል ኳርትዝ አፍሪካ ገልፆታል።
ሱዳን ትሪቡን በአንድ ወቅት የአድዋ ድልን አስመልክቶ ባስነበበው እትሙ በወቅቱ እጅግ ኋላ ቀር መሳሪያ የታጠቀው የኢትዮጵያ ጦር በአስገራሚ ወኔ በጊዜው ገንዘብ ሊገዛው የቻለውን መሳሪያ የታጠቀውን የጣሊያን ጦር ማሸነፉን ፅፏል። በጣሊያን በኩል ሙትና ቁስለኛ የሆነውን ሃይል ሱዳን ትሪቡን ሟቾቹን 7ሺ እንዲሁም ቁስለኞቹን ደግሞ 1ሺ500 መሆናቸውን ይገልፅና 3ሺዎቹ መማረካቸውን ፅፏል። እኤአ በ1896 ዓ.ም የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት ያሳየው የአድዋ ድል የወራሪው የጣሊያን ጦር በሁለቱም የአለም ጦርነቶች ሽንፈትን እንዲከናነብ ጥላውን እንዳጠላበትም ጋዜጣው አክሏል።
የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ በያመቱ ሜይ 25 በሚከበረው የአፍሪካ ቀን ጉባኤ ላይ ተገኝተው ስለ አድዋ በአል ምስክርነታቸውን ሲሰጡም የአድዋ ጦርነት የኢትዮጵያ ነፃነት እንዲቀጥል ከማድረጉም ባሻገር ሀገሪቷ በወቅቱ በቅኝ ግዛት እንደተያዙት ሃገራት እንዳልሆነች ያሳየችበትም ጭምር እንደሆነ የገለፁበት ሁኔታ በአፅንኦት ሊጠቀስ የሚገባው ነው።
“የበርሊኑ ጉባኤ አፍሪካ በቅኝ አገዛዝ ውስጥ መውደቅ እንዳለባት ሲወስን ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አፍሪካ በቅኝ ግዛት ቀንበር መያዝ የለባትም አሉ፤ተሳካላቸውም’’ ነበር ያሉት ምቤኪ ተሰብሳቢውን ባስደመሙበት ንግግራቸው።
የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በአድዋ ድል ክብረ በአል ላይ በተገኙበት ወቅት በአድዋ ድል በአል አከባበር ስነ ስርአት ላይ በመገኘታቸው ብቻ ክብር እንደሚሰማቸው ተናግረው ለድል በአሉ ምን አይነት ክብር መስጠት እንዳለባቸውም እንዲህ ብለው ነበር።
“…ጫማዬን ማውለቅ ይኖርብኛል ምክንያቱም ይህ የተቀደሰ ስፍራ ነው።አድዋ የአፍሪካ የተቀደሰ መሬት ነው።አድዋ የአፍሪካን የውርደት ሸማ የገፈፈ ነው።አፍሪካ በውጭ ወራሪ ሃይል ተወራ በቅኝ ግዛት ተይዛ ነበር ብለው የሚያስቡ ሰዎች ሃፍረት ሊሰማቸው ይገባል።” ነበር ያሉት።
የአድዋ ድል መሰል ምስክርነቶች ሲያንሱት እንጂ አይበዛበትም። ሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ከቅኝ ገዚዎች አገዛዝ የተላቀቁበትን የነፃነት ቀን ሲያከብሩ ለጥንት አባትና እናት አርበኞች ምስጋና ይግባቸውና እኛ ቅኝ ገዚዎችን ድል የነሳንበትን የአድዋ ድል በኣል እናከብራለን።
እነሆ በ123ኛው አመት የአድዋ ድል በአል አከባበር ወቅት ላይ ሆነን እኛስ ምን እያሰብን እንገኛለን። የአሁኑ ትውልድም ለመሰል ታሪኮች የሚመጥን አስተሳሰብና አመለካከትን በመያዝ በተለያዩ መስተጋብሮች የተጋመደውን የሃገራችን ማህበረሰብ ህልውና በተጠናከረ አንድነት ለማስቀጠል ከምንግዜውም በበለጠ መጣር ይጠበቅበታል።
የአድዋ ድል በአል ከዚህም በበለጠ የተቡ ብዕሮች ሊፅፉለት፣የሰሉ አዕምሮዎች ጥልቅ ጥናት ሊያደርጉበት፣ርቱዕ አንደበቶች ሊናገሩለት፣ አልፎ ተርፎም ምሁራኖቻችን አባቶቻችን ያሳዩት የህብረት ተጋድሎ እንዴት ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀን ሃይል ማንበርከክ እንደቻለ የሚተነትን ፍልስፍናን ለአሁኑ ትውልድ ጀባ ሊሉት ይገባል፤ እንላለን።