ቀጥታ፡

በወላይታ ሶዶ ከተማ በህገ-ወጥ ቤቶች ላይ ህግን ለማስከበር እየሰራ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ

ሶዶ የካቲት 22/2011 በወላይታ ሶዶ ከተማ በህገ-ወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶችን በራሳቸው በማያፈርሱት ላይ ህግን የማስከበር ሥራ እያከናወነ መሆኑን የወላይታ ሶዶ ዞን ፖሊስ አስታወቀ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ለሚናፈሱ የተሳሳቱ ወሬዎች ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስቧል።

የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ኤፌሶን ላካይቶ እንዳሉት በሶዶ ከተማ ህጋዊ አሰራርን ሳይከተሉ የተገነቡ ቤቶችን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ህዝብን ባሳተፈ መልኩ የማፍረስና ህግን የማስከበር ተግባር እየተከናወነ ነው፡፡

በዚህ ሂደትም ከአስተዳደሩ ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረት ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ቤቶችን ባለቤቶቹ በራሳቸው በማንሳት ላይ የሚገኙ ሲሆን ፈቃደኛ ባልሆኑት ላይ የጸጥታ ኃይሎች ከአፍራሽ ግብረኃይል ጋር በመሆን ህግን የማስከበር ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት የካቲት 18 ቀን 2011ዓ.ም ልዩ ስሙ "ሁምቦ ላሬና" በሚባል ቀበሌ ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ገደማ አንድ ነዋሪ በራሱ ፈቃድ ቤቱን ለማፍረስ ሲሞክር ድንገት አዳልጦት መውደቁን ገልጸዋል።

ጉዳት የደረሰበት ግለሰብ ከሁለት ቀን በኋላ ለህክምና ወደሆስፒታል ቢመጣም ህይወቱን ማትረፍ እንዳልተቻለ በፖሊስ በኩል መረጋገጡን ምክትል ኮማንደር ኤፌሶን ተናግረዋል።  

ከዚህ ውጭ በጸጥታ ኃይል አባላት ላይ የደረሰ ጉዳትም ሆነ ሌላ የሞተ ሰው አለመኖሩን ነው የተናገሩት፡፡

በዚሁ መነሻም የካቲት 20 ቀን 2011ዓ.ም በግምት ከቀኑ 6፡00 ሰዓት አካባቢ የሟቹ ቤተሰብና ዘመድ ከሆስፒታል ወደቤት ሲመለሱ በከተማው አዲሱ መናኸሪያ ጋር ሲደርሱ በህገወጥ ተግባር መክበርን የለመዱ ግለሰቦች ሁከት ለመፍጠር መሞከራቸውን ገልጸዋል።

ግለሰቦቹ ምንም ለማያውቁ ህጻናት ገንዘብ በመስጠት ጎማ ለማቃጠልና መሰል ተግባር ለመፈጸም ቢሞክሩም በህዝቡና በጸጥታ ኃይሎች የተቀናጀ ጥረት መክሸፉን ገልጸዋል፡፡

ህብረተሰቡ ባደረገው ጥቆማ ሆን ብለው ነውጥ ለመፍጠር ሲሰሩ የነበሩ 27 ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው በአሁኑ ወቅት ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ምክትል ኮማንደር ኤፌሶን እንዳሉት ህዝብን ያሳተፈ ህግን የማስከበር ሂደት ያለምንም ችግር ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ከተማዋም በተለመደው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ናት፡፡

"ይሁንና በሟች ግለሰብ ላይ አደጋው የደረሰው ጠዋት ከመሆኑም በላይ በወቅቱ የትኛውም የጸጥታ ኃይል በለሌበት የተፈጠረውን ክስተት አንዳንድ መገናኛ ብዙሀንና የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከእውናታው ውጭ በመዘገብ የህዝቡንና የከተማውን ገጽታ ለማበላሸት ጥረት እያደረጉ ነው" ብለዋል፡፡

"የህግ ማስከበሩን ተግባር ለማስተጓጎል ያሴሩና በህገወጥነት ተግባሩ ተጠቃሚ የነበሩ ጉዳዩን ከጸጥታ ኃይል ጋር በማላከክ ትርፍ ለማግኘት እየሰሩ መሆናቸውንም ተረድተናል፤ ሊታረምም ይገባል" ብለዋል ምክትል ኮማንደር ኤፌሶን፡፡

"በሀሰት ወሬ ህዝብን ለማወክ የተሳሳተ መረጃ የሚሰጡና የከተማውን ገጽታ ለማበላሸት የሚሠሩ ኃይሎች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባልም" ሲሉም አሳስበዋል፡፡

ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር የህግ የበላይነትን አቅም ለማሳጣት የሚጥሩትን በማጋለጥ በኩል ህዝቡ ከፖሊስ ጋር የጀመረውን ትግል እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም