ቀጥታ፡

አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ በ83 ዓመቱ አረፈ

አዲስ አበባ የካቲት 22/2011 አንጋፋው የሙዚቃ፣ የቴአትር ፀሐፊና የተውኔት ባለሙያ አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ በ83 ዓመቱ ዛሬ የካቲት 22 ቀን 2011 ዓ.ም አረፈ።

አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ በኦሮሚያ ክልል አዲስ ዓለም ደብረ-ፅዮን ቅድስት ዓለም ማርያም ልዩ ስሙ ነጋዴ ሠፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሚያዝያ 20 ቀን በ1928 ዓ.ም ተወለደ።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በትውልድ መንደሩና በአዲስ አበባ ተስፋ ኮከብ ትምህርት ቤት እንደተማረ የግል ማህደሩ ያስረዳል።

አርቲስት ጌታቸው ሥራ የጀመረው በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ የቴአትርና የሙዚቃ ማስፋፊያ ክፍል ነበር።

የግርማዊ ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የዘውድ በዓል ዝግጅትን ምክንያት በማድረግ በአፄ ኃይለሥላሴ ትዕዛዝ ጥቅምት 23 ቀን 1948 ዓ.ም ወደ ብሔራዊ ትያትር ቤት ተዛውሯል። 

አርቲስት ጌታቸው ለበርካታ ሙዚቀኞች የዘፈን ግጥም የሰጠ ሲሆን በጡረታ እስከተገለለበት ግንቦት 1 ቀን 1982 ዓ.ም ድረስ በቴአትር በትወና እና በማማከር ሲሰራ ቆይቷል።

በተለይ ሀሁ በስድስት ወር፣ የከርሞ ሰው፣ ጠልፎ በኪሴ፣ የፌዝ ዶክተር፣ ዋናው ተቆጣጣሪ እና በሌሎችም የመድረክ ቴአትሮች ላይ ተሳትፏል።

አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ በ1994 ዓ.ም የህይወት ዘመን ሽልማት የ20 ሺህ ብር ተሸላሚ የነበረ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከሦስት ዓመት በፊት የአርቲስቱን 80ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የጥበብ ሥራዎቹን ዘክሯል። 

አርቲስት ጌታቸው የሁለት ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበር።

የቀብር ስነ-ስርዓቱ የካቲት 24 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ ስድስት ሰዓት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ወዳጅ ዘመድና የጥበብ አድናቂዎቹ በተገኙበት ይፈጸማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም