በትግራይ ደቡባዊ ዞን ያገገሙ አካባቢዎች ለገቢ ማስገኛነት እየዋሉ ነው

66

ማይጨው የካቲት 22/6/2011 በትግራይ ደቡባዊ ዞን በተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ ያገገሙ አካባቢዎችን ለገቢ ማስገኛነት በማዋል ተጠቃሚ መሆናቸውን አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣት አርሶ አደሮች ገለጹ።

የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ በበኩሉ በዞኑ ሕዝብ ጉልበት የለሙት ተፋሰሶች ለ45 ሺህ ወጣቶች ሥራ መፍጠራቸውን አስታውቋል።

የእንዳመኾኒ ወረዳ ነዋሪው ወጣት ስዩም ግርማይ እንዳለው ላለፉት አራት ዓመታት ከሌሎች 30 ወጣቶች ጋር ተደራጅቶ የጠረጴዛ እርከን በተሰራበት መሬት ላይ በመስኖ ልማት ተሰማርተው ተጠቃሚ ሆነዋል።

"ምንጮችን በመጥለፍና የውሃ ማሰባሰቢያ በመገንባት አፕል፣ ጌሾ፣ ነጭ ሽንኩርትና ሌሎች ተክሎችን በዓመት ሁለት ጊዜ እያመረትን ተጠቃሚ ሆነናል"  ሲልም አስተያየቱን ገልጿል።

ከምርቱ ሽያጭ በዓመት እስከ 300 ሺህ ብር ድረስ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን የጠቆመው ወጣት ስዩም ከገቢው 30 በመቶውን በጋራ እንደሚቆጥቡ ተናግሯል።

''የጠረጴዛ እርከን ሥራ የኑሮአችን መሠረት ነው'' ያለው ወጣት ስዩም፣ እርከኑን ከመጠገን ባለፈ የደን ጭፍጨፋን በመከላከል ላይ መሆናቸውን ተናግሯል።

የቤተሰቡን የእርሻ ሥራ በማከናወንና በትርፍ ጊዜውም በጉልበት ሥራ በመሰማራት ከቤተሰቡ ጋር ይኖር እንደነበር የገለጸው ደግሞ በአላጀ ወረዳ የአጸላ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ህሉፍ ታደሰ ነው።

ወጣቱ በአሁኑ ወቅት ደን በሚለማባቸው ቦታዎች ከ30 ወጣቶች ጋር ተደራጅቶ በንብ ማነብ ሥራ መሰማራታቸውን ገልጿል።

በዚህም ዓመት ከ40 ቀፎዎች ከሚያመርቱት ማር ከ200 ሺህ ብር በላይ ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግሯል።

"በደን ልማት ዘርፍ በመሰማራት ተጠቃሚ ሆነናል" የሚለው ደግሞ በዚሁ ወረዳ የሰሳት ገጠር ቀበሌ ነዋሪ  ወጣት መሐሪ ታደለ ነው፡፡

ከሦስት ዓመታት በኋላ ለቆረጣ የደረሰውን ባህር ዛፍ ለማይጨው ፓርቲክል ቦርድ ፋብሪካ በመሸጥ ግማሽ ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘታቸውን ተናግሯል፡፡

በዞኑ ግብርና ገጠር ልማት መምሪያ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማት ሥራ ቡድን መሪ አቶ አቻምየለህ አሰፋ በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ ሕዝብ ጉልበት የለሙት ተፋሰሶች ለ45 ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አስችለዋል።

አቶ አቻምየለህ እንዳሉት በየዓመቱ ከ9 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የሚካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ተደርጓል።

ከአራት ዓመታት ወዲህ ያገገሙ ተፋሰሶችን በመለየትና በመከለል ለአካባቢው ወጣት አርሶ አደሮች የሥራ ዕድል እየፈጠሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ወጣቶቹ  ገቢያቸው ከሚያጠናክሩባቸው መስኮች መካከል የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በደን ክልል ውስጥ የደን ልማት፣ የእንስሳት ማድለብና እርባታ ሥራዎች ይገኙባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም