የአድዋ ድል ለፓን-አፍሪካን ንቅናቄ ስኬት መሠረት ጥሏል- የታሪክ ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል ለፓን-አፍሪካን ንቅናቄ ስኬት መሠረት ጥሏል- የታሪክ ምሁራን
አዲስ አበባ የካቲት 22/2011 ኢትዮጵያዊያን በ1888 ዓ.ም የአድዋ ጦርነት በጣሊያን ላይ ያስመዘገቡት ድል ለፓን አፍሪካን ንቅናቄ ስኬት መሠረት የጣለ መሆኑን የታሪክ ምሁራን ገለጹ።
ኢዜአ በአድዋ ድልና በጥቁር ህዝቦች መካከል ስላለው ግንኙነት ያነጋገራቸው የታሪክ ምሁራን እንደገለጹት ጥቁር ህዝቦች የጀመሩት የነጻነት ትግል ፍሬ ማፍራት የጀመረውና የተጠናከረው ኢትዮጵያዊያን ጣሊያንን ድል ካደረጉበት ማግስት ጀምሮ ነው።
በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አልማው ክፍሌ እንዳሉት በ1900 የፓን አፍሪካን ንቅናቄን የጀመሩትን ጥቁር ታጋዮች ህዝባዊ ንቅናቄ ለማቀጣጠልና ደጋፊዎችን ለማግኘት የአድዋን ድል መሳሪያ አድርገው ተጠቅመዋል።
''ከቅኝ አገዛዝና ከባርነት ነጻ መውጣት ይቻላል፣ ነጮችን ማሸነፍ ይቻላል። በማለት ለጥቁሮች የተደራጁ ጥሪ ያቀረቡት ከአድዋ ድል መመዝገብ በኋላ ነው'' ብለዋል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ እውነቱ በላቸው በበኩላቸው በአፍሪካ የፀረ ቅኝ ግዛት ተጋድሎ ያቆጠቆጠው ከአድዋ ድል በኋላ መሆኑን ገልጸዋል።
ድሉ ለፓን አፍሪካን ንቅናቄ ያደረገው አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ቡድን መሪ ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ በበኩላቸው ''በሁሉም ነገር ነጮች የበላይ ናቸው'' የሚለውን አስተሳሰብ ማፍረስ የቻለው የአድዋ ድል እንደሆነ አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር ሳሙኤል ነጋሽም የአድዋ ድል ''ነጭ በጥቁር ሊሸነፍ አይችልም'' የሚለውን አስተሳሰብ የቀየረ ታሪክ መሆኑን ገልጸዋል።
በአድዋ ላይ የተገኘው ድል የፈጠረው ስሜት የፓን አፍሪካን ንቅናቄ እንደወለደ ነው ዶክተር ሳሙኤል ያስረዱት።
የአድዋን ድል ተከትሎ መላው ጥቁር ህዝብ የጀመረው የነጻነት ትግል ፍሬ አፍርቶ ዛሬ ላይ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ነጻነታቸውን ለማግኘት በቅተዋል።
ምንም እንኳን ከቀድሞ ቅኝ ገዢዎች የተለያዩ ተፅዕኖዎች ሙሉ በሙሉ ተላቀዋል ባይባልም ሉዓላዊ አገር ሆነው የራሳቸውን ፖሊሲ ነድፈው ህዝባቸውን ከድህነትና ኋላ ቀርነት ለማውጣት ጥረት እያደረጉም ይገኛሉ።