ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 9ኛውን ቦይንግ 737-800 የጭነት አውሮፕላን ተረከበ

አዲስ አበባ  የካቲት 22/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ 9ኛውን  ቦይንግ 737-800 የጭነት አውሮፕላን ዛሬ ተረከበ።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ከዚህ ቀደም የነበሩት የጭነት አውሮፕላኖች የአገልግሎት ጊዜ ረዥም በመሆኑ እነርሱን ከአገልግሎቱ በማስወጣት ዘመናዊና ነዳጅ ቆጣቢ በሆኑት የመተካት ተግባር አየተከናወነ ነው።

አየር መንገዱ ዛሬ የተረከበውና በአንድ ጉዞ   ከ23 ሜትሪክ ቶን የመጫን አቅም ያለው ይህ ዘመናዊ የጭነት አውሮፕላንም ኢትዮጵያ ወደውጭ አገራት ለምትልከው የሥጋና የአትክልት ምርቶች ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።

አየር መንገዱ የጭነት አውሮጵላኖችን በዘመናዊ የቦይንግ ምርቶች ከመተካቱም ባሻገር የገበያ ትስስር ከመፍጠር አኳያ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ከአውሮፓ የሚያስገቡትን ምርቶች ከኢትዮጵያ እንዲያስገቡ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለዋል። 

አየር መንገዱ አዲሱን ቦይንግ 737_800 የጭነት አውሮፕላን ያስገባው በረዥም ጊዜ ኪራይ ሲሆን የመንገደኛ  የነበረውን አውሮፕላን ወደ ጭነት አውሮፕላን የመቀየር ስራ ከአየር መንገዱ ጋር መሰራቱም ተመልክቷል።

በአሁኑ ሰዓት አየር መንገዱ በዓመት 400 ሺህ ቶን ጭነት የማጓጓዝ አቅም ያለው ሲሆን አሜሪካና አውሮፓን ጨምሮ በአፍሪካ፣ በባህረ ሰላጤው፣ በመካከለኛው ምስራቅና በኢሲያ አገራት 44 መዳረሻዎች አሉት።

በመጪዎቹ ስድስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የጭነት መጠኑን አሁን ካለበት ከእጥፍ በላይ የማሳደግ እቅድ አለው ተብሏል። ከዚህም ሌላ አየር መንገዱ መዳረሻውን ወደ57 አገራት በማሳደግ በየዓመቱ ሁለት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ትርፍ የማግኘት ራአይ ሰንቆ እየሰራ እንደሆነም

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም