አስተዳደሩ ከፍተኛ ብክነት ሲፈጥሩ የነበሩ የአሰራር ግድፈቶችን እያስተካከለ መሆኑን ገለጸ

59

አዲስ አበባ የካቲት 22/2011 ከፍተኛ የህዝብና የመንግስት ገንዘብን ለብክነት ሲዳርጉ የነበሩ የአሰራር ግድፈቶችን እያስተካከለ መሆኑን የብሄራዊ ቤተ-መንግስት አስተዳደር አስታወቀ።

አስተዳደሩ የ2011 ግማሽ አመት የስራ አፈፃፀሙን ዛሬ ሲገመግም ቀደም ሲል በነበሩ የአሰራር ግድፈቶች በስልክ መስመር፣ በምግብና መጠጥ እንዲሁም በተለያዩ የንብረት አያያዝ ችግሮች ከፍተኛ ገንዘብ መባከኑን አስታውቋል።

ለአብነትም ከአሁን በፊት በብሄራዊ ቤተ-መንግስት ስም ወጥተው በአገልግሎት ላይ ከነበሩት 300 የስልክና የኢ-ቪዲዮ መስመሮች ውስጥ 38 ብቻ ተቋሙ የሚጠቀምባቸው መሆኑ ተረጋግጧል።

የቤተ-መንግስት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ እንዳሉት የስልክና የኢ-ቪዲዮ መስመሮቹ ለአንዳንድ ባለስልጣናት የግል ጥቅም ይውሉ እንደነበርና በዚህም በዓመት ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ሲባክን እንደነበር ተናግረዋል።

የቤተ-መንግስት አስተዳደር ከንብረት አያያዝ፣ ከገንዘብ አጠቃቀምና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ኮሚቴ አቋቁሞ ጥናት ማካሄዱንና ከሚጠቀምባቸው 38 መስመሮች ውጭ ቀሪዎቹ እንዲዘጉ ማድረጉን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም አንዳንድ ባለስልጣናት ከቤተ መንግስት ውድ መጠጦችና ምግቦችን በመጫን ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ይባክን እንደነበር ጠቅሰዋል።

በዚህ ተግባር የተሳተፉትን ግለሰቦች ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን የመለየትና ለህግ የማቅረቡን ስራም እንቀጥላለን ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ክምችት ክፍል ያለው እቃ ሳያልቅ አዲስ ግዥ የማካሄድ፣ የነበሩ እቃዎችን በአግባቡ አለማስቀመጥም ሌላው ለብክነት በር የከፈተ አሰራር ነበር ሲሉ ተናግረዋል።

ዳይሬክተሯ እንዳሉት የቤተ-መንግስት አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት እነዚህን አሰራሮች እያስተካከለ የሚወገዱትን ንብረቶች የማስወገድ፣ በቅርስነት መቀመጥ ያለባቸውን የማስቀመጥና ለአገልግሎት የሚውሉትን ደግሞ በአይነት በማደራጀት ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም