ወጣቱ ትውልድ ከአድዋ ድል አንድነትን በመማር ከእርስ በእርስ ግጭት ሊላቀቅ አንደሚገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ ትውልድ ከአድዋ ድል አንድነትን በመማር ከእርስ በእርስ ግጭት ሊላቀቅ አንደሚገባ ተጠቆመ
ደብረ ብርሀን/ማርቆስ የካቲት 22//2011 ወጣቱ ትውልድ ከአድዋ ድል አንድነትን በመማር ከእርስ በእርስ ግጭትና ከዘር ፖለቲካ ተላቆ ለሀገሩ እድገት በጋራ መስራት አለበት ሲል ጋዜጠኛ አበበ ገላው ተናገረ፡፡
123ኛው የአድዋ ድል በዓል ዛሬ በደብረ ብርሃንና በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በፓል ውይይት ተከብሯል፡፡
የኢትዮጵያ ሳተላይት ሬዲዮና ቴሌቨዥን ጣቢያ ጋዜጠኛና የቦርድ አባል አበበ ገላው በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የዓድዋ ድል በዓል ሲከበር እንዳለው ወጣቱ ትውልድ በዓሉን ሲያከብር ከዘር ፖለቲካና ከእርስ በእርስ ግጭት ወጥቶ ሊሆን ይገባል፡፡
"ጥንት አባቶቻችን ጠላትን ሊያሸንፉ የቻሉት በአንድነት አስተሳሰብ እንጂ በዘር፣ በቋንቋና በአመለካከት ተከፋፍለው አይደለም" ያለው ጋዜጠኛ አበበ፣ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የሚስተዋሉ ግጭቶችን ወጣቶች ሊቃወሙ እንደሚገባ አመልክቷል፡፡
"ባለፉት ወራት የታየው ሀገራዊ ለውጥ ዳር እንዲደርስ ወጣቶች በአንድነት በመቆም በጋራ መምከርና በአስተውሎ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል" ሲልም ገልጿል፡፡
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኃይለማሪያም ብርቄ በበኩላቸው "ዘንድሮ የዓድዋን ድል የምናከብረው የኢትዮጵያ ትንሳኤ ዋዜማ ላይ ተገኝተን በመሆኑ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል" ብለዋል፡፡
የዓድዋ ድል በዓል በኢትዮጵያና በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ እንዳለው ገልጸው ድሉ የኢትዮጵያ ስልጣኔ የነበረውን የራሱን መንገድ ሳይለቅና አዲሱንም ሳይንቅ እንዲጓዝ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በዓሉ እስከ መጪው ግንቦት ወር ድረስ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚቀጥል የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ የታሪክ ሙሁራን ጥናታዊ ጽሁፍ በማዘጋጀት የአድዋንና ተያያዥ ታሪኮችን ለማስተዋወቅ እንዲረባረቡ አመልክተዋል፡፡
በደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ኢንጂነሪንግ ድፓርትመነት የ4ኛ ዓመት ተማሪ ሳህለአምላከ ከፍያለው በበኩሉ "በዘንድሮ በዓል የተደበቁ ብዙ የሀገሪቱን ታሪኮች አውቂያለሁ" ብሏል።
በዓሉን ማክበር ብቻውን በቂ ባለመሆኑ በቀጣይ እውነታ ላይ የተመሰረተ ታሪክ ለትውልድ ለማስተላለፍ የድርሻውን እንደሚወጣ አረጋግጧል።
"የአድዋ ድል ለዘመናት በአብሮነት የገነባናቸውን ሀገራዊ እሴቶች የበለጠ የሚያጠናክር ታሪካዊ ክስተት ነው" ያሉት ደግሞ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በዓሉ ሲከበር የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ ናቸው፡፡
"ተማሪዎች የሀገራቸውን አኩሪ ታሪክና የአያቶቻቸውን ተጋድሎ በመረዳት ሀገራዊ ፍቅርና አንድነት እንዲነግስ በአስተውሎ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል" ብለዋል፡፡
በበዓሉ ላይ “የአድዋ ድል ምስጢር” በሚል ርዕስ ጥናት ያቀረቡት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻው በበኩላቸው ጣሊያኖች የኢትዮጵያዊያንን የአንድነት መንፈስ ባለመረዳታቸው ጥረታቸው ከንቱ ሆኖ የጥቁር ህዝቦች ነጻነት መረጋገጡን ገልጸዋል።
"የዛሬው ትውልድም ታሪኩንና ሀገሩን በማልማት ዳግም ታሪክ ሰርቶ የኢትዮጵያን እድገትና ስልጣኔ የማይሹ ኃይሎችን ማሳፈር ይኖርበታል" ብለዋል።
" የአድዋ ድል ለሀገር ፍቅር እና አንድነት " በሚል መሪቃል በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው አውደ ጥናት ላይ የተሳተፈው ተማሪ ሀብተወልድ ልኡል በበኩሉ የአድዋ ድል ለወጣቱ የአንድነት ስንቅ መሆኑን ተናግሯል።
ጥንታዊ ጀግኖች አባቶች እርስ በእርስ በመተሳሰባቸውና ለአንድነታቸው በነበራቸው ጽኑ እምነት ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን የኢጣሊያ ጦር አሸነፈው ነጻነቷና ክብሯ የጠበቀች ሀገር ማስረከባቸውን አስታውሷል።
"የዛሬው ትውልድ ከመከፋፈል ምንም ትርፍ እንደማይመጣ ተገንዝበን እርስ በእርስ በመከባበርና በመደጋገፍ አባቶች ያስረከቡንን ነጻ ሀገር የበለጠ ማልማትና ታሪካዊ ማድረግ ይኖርብናል" ብሏል ።
በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች በተካሄደው ውይይት ተማሪዎች፣ ጥሪ የተደረጋላቸው እንግዶችና የዩኒቨርሲቲውዎቹ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል፡፡