የአድዋን የተጋድሎ ታሪክ በሳይንሳዊ ምርምርና በጥበባዊ ስራዎች ማድመቅ ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋን የተጋድሎ ታሪክ በሳይንሳዊ ምርምርና በጥበባዊ ስራዎች ማድመቅ ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ
አዲስ አበባ የካቲት 22/2011 የአድዋ የተጋድሎ ታሪክ በዓለም ፊት ተገቢውን ቦታ እንዲሰጠው በሳይንሳዊ ምርምርና በጥበባዊ ስራዎች ማድመቅ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ 123ኛውን የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል አስመልክተው ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን በወራሪ የጣሊያን ጦር ላይ የተቀዳጁት ድል ፖለቲካዊ ነጻነታችን ታፍሮና ተከብሮ እንዲኖር ያስቻለ 'ደማቅ የታሪክ አሻራ ነው' ብለዋል።
ጀግኖች የተቀዳጁት ድል ከአገር አልፎ ለመላው አፍሪካ ብሎም በባርነት ቀንበር ይማቅቁ ለነበሩ መላው የዓለማችን ሕዝቦች ተስፋን የፈነጠቀ ነው።
ይህ አኩሪ ታሪክ በዓለም ፊት ተገቢውን ቦታ እንዲይዝ በጥበብ በአካዳሚያዊ ፈለግና በማህበረ ባሕላዊ ዐውድ መመርመር፣ ማክበርና ማጥናት ያስፈልጋልም ብለዋል።
ለዚህም ምሁራንና የጥበብ ሰዎች ዓለም አቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ ስራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበው መንግስት የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዓሉን አስመልክተው ያስተላለፉት ሙሉ ቃል ይህ ነው።
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዐቢይ አሕመድ፣ የ123ኛው የዐድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን በተመለከተ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተላለፉት መልእክት
በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በሙሉ ለመላው አፍሪካውያንና ለዓለም ነጻነት ወዳድ ሕዝቦች ሁሉ በየዓመቱ የካቲት 23 ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች በታላቅ ድምቀት ለምናከብረው ለ123ኛው የዐድዋ ድል መታሰቢያ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን፡፡
ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን እናቶቻችን እና አባቶቻችን በወራሪው የጣልያን ጦር ላይ በዐድዋ የተቀዳጁት ታላቅ ወታደራዊ ድል፣ በኢትዮጵያ ምድር የኢትዮጵያ እንጂ የቅኝ ገዢ ሮማ ባንዲራ እንዳይውለበለብ ያደረገ ብቻ ሳይሆን፣ ፖለቲካዊ ነጻነታችንም ከዘመን ዘመን ታፍሮና ተከብሮ እንዲኖር ያስቻለ ደማቅ የታሪክ አሻራ ጭምር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በዐድዋ ላይ በደምና በአጥንት የከፈሉት መሥዕዋትነት የዛሬው እና የነገው ትውልድ በቅኝ ግዛት ቀንበር ትከሻው ጎብጦ አንገቱን ደፍቶ እንዳይኖር አስችሎታል፡፡ የዐድዋው ድላችን ቀንተንም - ነቅተንም በዓለም ፊት ለመቆማችን አባቶቻችን ያቀዳጁን አክሊል ነው፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፣ በወራሪውና በተስፋፊው የኢጣልያ ጦር ላይ ጀግኖቹ እናቶቻችንና አባቶቻችን የተቀዳጁት ድል ከራሳችን ነጻነት ባሻገር ለመላው አፍሪካ ብሎም በባርነት ቀንበር ይማቅቁ ለነበሩ መላ የዓለማችን ሕዝቦች ሁሉ ተስፋ የፈነጠቀ እና ወኔ ያሰነቀ ታሪካዊ ክሥተት ነው፡፡ ይህን በውል ለመረዳት መቻል ትናንታችንን ዘክረን፣ ዛሬን መርምረን፣ ነጋችንን ለመቃናት ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ የዐድዋው ድላችን ወደ ሌሎች ድርብ ድርብርብ ድሎች መሻገሪያችን፤ የድካም መርቻ ጉልበታችን፤ በዝለት ጊዜም መበርቻችን ነው፡፡ ለዚህም ከዐድዋ ድላችን ወዲህ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የተቀዳጀናቸው ስኬቶቻችን ህያዋን ምስክሮች ናቸው፡፡
የዛሬው ትውልድም እንደ አባት እናቶቹ - እንደ አያት ቅድመ አያቶቹ ሁሉ የሚገጥሙትን ፈተናዎች እና የሚያደናቅፉትን ተግዳሮቶች በድል በመወጣት የአባቶቹና የእናቶቹ ልጅ መሆኑን በተግባር የሚያረጋግጥበት ታሪካዊ የዘመን አንጓ ላይ ቆሟል፡፡
ዐድዋ ከትግል እና ድል የሚሻገር የተጨቋኞች ረቂቅ ኃይል ነው፡፡ ዐድዋ መልከ ብዙ ትርጓሜና ሕይወታዊ አስተምህሮ በውስጡ አቅፎ የያዘ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ፍልስፍና ነው፡፡ በፈተናጊዜ፣ ህልውና አደጋ ላይ በወደቀ ጊዜ፣ የመደመር መንፈስና ንቅናቄ አንድን ሕዝብ ሊያደርስበት የሚችለውን የልዕልና ጫፍ ያየንበት ነው፡፡
ዐድዋ ኢትዮጵያውያን ከመሐልና ከዳር እንዲሁም የማንነታቸውን ልክ ያሳዩበት የመሥዕዋዕትነታቸው ውጤት ነው፤ ዐድዋ እኛ ነን፡፡ አትንኩኝባይነት - ጸዳላችን፣ የሀገረ ፍቅር ስሜት - ጥበባችን፣ ለአንድ ዓላማ መጽናት - ጥለታችን፣ጀግንነትና ነጻነት ወዳድነት ደግሞ - የራስ ቁራችን ሆኖ የዋልንበት - እኛ ማለት ዐድዋ ነን፡፡
የሀገር መሪዎቻችን ሕዝብን የማስተባበር ችሎታ፣ የጦር ጄኔራሎቻችን የጦር አመራር ጥበብ፣የዲፕሎማቶቻችን የዲፕሎማሲ ልቀት የታየበት የጥቁር ሕዝቦች የፀረ ኮሎኒያሊዝም ገድል ነው ዐድዋ፡፡
የዐድዋ ድል የሴት ኢትዮጵያውያን የዐርበኝነት ተጋድሎና የላቀ ሚና መገለጫ ነው፡፡ እኅቶቻችንና እናቶቻችን ከስንቅ ዝግጅት እስከ ጦር መሪነት፣ በግጥምና ዜማ ዐርበኞቹን ከማጀገን እስከ ቁስለኛ ተንከባካቢት፣ ከትጥቅ አቀባይነት እስከ ምርኮ ሰብሳቢነት፣ የተሰለፉበት ደማቅ ዐደባባይነው - ዐድዋ፡፡ የዐድዋን ድል የሚያከብር ሕዝብ የሴቶች ክብር የገባው መሆን አለበት፡፡
ዐድዋ መሪ እና ተመሪ - አስተዳዳሪ እና ተዳዳሪ ሲደማመጡ፣ ሲግባቡና ለአንዲት ሀገር ሲሠሩ የሚበግራቸው ነገር እንደማይኖር አስተምሮን ያለፈ ታሪክ ነው፡፡ የክብርህ መመኪያ- ደስታ እና ሕይወትህ የሆነችውን ውብ ሀገር ከወራሪ ትታደግ ዘንድ የምሥራቅ - የምዕራብ- የሰሜን እና የደቡብ ሰው ፊትህን ወደ ዐድዋ አዙረህ ወረኢሉ ላይ ቆየኝ ያለውን የመሪውን የዐፄ ምኒልክንቀጠሮ አክብሮ ለነፍስ ቀጠሮ በነፍስ የደረሰ ሳተና ሕዝብ፣ የድል አክሊል የተቀዳጀበት ታሪካዊ ቀን ነው - ዐድዋ፡፡
በዛሬው ዕለት የዘንድሮውን የድል በዓል ስናከብር እንደዚህ ዘመን ነዋሪና እንደ አዲስ ትውልድ፣በድሉ ውስጥ የተካተተውን ሰምና ወርቅ፣ ምሥጢርና ቅኔ በጥልቀት በመረዳት መሆን ይኖርበታል::
"ነገረ ዐድዋን በጥበብ፣ በአካዳሚያዊ ፈለግ እና በማኅበረ ባሕላዊ ዐውድ መመርመር- ማክበር እና ማጥናት ያስፈልገናል፡፡ "
በትክክል ታሪክን ለሚመረምር ትውልድ ዐድዋ ውስጥ - ህልውናን አጽንቶ የመኖር፤ ዐድዋ ውስጥ- ዲፕሎማሲ፣ ዐድዋ ውስጥ - ወታደራዊ ስትራቴጂ፣ ታላቅ ውስጣዊ የሕዝቦች ኅብረትና አንድነት፣ጥበብ እና ተግባቦት፣ ፍቅር እና መስጠት፣ ክብር እና ጀግንነት መልቶና ሰፍቶ የነበረ መሆኑንእናያለን፡፡ አንድን ሀገራዊ ድል ለማስመዝገብ የሁሉንም አካላት ተሳትፎ የግድ እንደሚልእንማራለን፡፡ የሀገር መሪዎች፣ የጦር አበጋዞች፣ ቃፊሮች፣ ወታደሮች፣ ስንቅ አዘጋጆች፣ ሐኪሞች፣አዝማሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ እንጨት ፈላጮች፣ ውኃ ቀጅዎች፣ የጥበበ እድ ባለሞያዎች፣ታሪክ መዝጋቢዎች፣ ሌላው ቀርቶ ከብቶችና አጋሠሶች እንኳን ሳይቀሩ ለድሉ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ አድርገዋል፡፡ መደመር ማለት ይሄ ነው፡፡
"የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን እንደ ትናንቶቹ ኢትዮጵያውያን በሕይወት መሥዋዕትነት ብቻ ሳይሆን እየኖርን በመሥራት፣ በደም የተቀበልናትን ሀገር ነጻነቷን ጠብቀን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ጠንክረን መታገል ይገባናል፡፡"
በጦር መሣሪያ ዐቅም፣ በሀብት፣ በወታደራዊ አደረጃጀት እና በዘመናዊ የጦር ስልት በወቅቱ ታላቅ ደረጃ ደርሻለሁ ብሎ ያሰበውን የኢጣሊያ ወራሪ ጦር ከዚያ በፊት ባልታየና በታሪክ ውስጥ ባልተስተዋለ ጀግንነት፣ ዐርበኞች እናቶቻችንና አባቶቻችን ድል የመቀዳጀታቸው እና የማሸነፋቸው ቁልፍ ምሥጢር ውስጣዊ ልዩነታቸውን አቻችለው በኅብረትና በአንድነት ተደምረው፣ ለአንድ ሀገራዊ ግብ፣ በፍቅር መቆማቸው ነው፡፡ ብልህ ትውልድ ከዐድዋው የድል መሠዊያ ላይሊጭር የሚገባው ቁም ነገርም ይሄው ነው፡፡
የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን እንደ ትናንቶቹ ኢትዮጵያውያን በሕይወት መሥዋዕትነት ብቻ ሳይሆን እየኖርን በመሥራት፣ በደም የተቀበልናትን ሀገር ነጻነቷን ጠብቀን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ጠንክረን መታገል ይገባናል፡፡ በልዩነት ተቆራቁሰን እርስ በርስ የምንጫረስና የምንጠፋፋ ሳይሆን የውዲቷ ሀገራችንን ችግሮች ለመቅረፍ እንድንችል በኅብረትና በአንድነት፣ በፍቅርና በይቅርታ ወደፊት መራመድ ይጠበቅብናል፡፡ መሪና ተመሪ በሁሉም ጉዳዮች ባይግባቡ እንኳን የሀገርን ነጻነት፣ አንድነት፣ እኩልነት፣ ፍትሕና ዴሞክራሲን በተመለከቱ ጉዳዮች ግን ተግባብተውና አንድ ሆነው ከራሳቸው አልፎ ለሌላው የሚተርፍ ድል ያስመዘግባሉ- ዐድዋ ያስተማረን ይኼንን ነው፡፡
ዐድዋ ያስተማረን ሌላም ነገር አለ፡፡ በደምና በአጥንት የተጠበቀው ነጻነት ከሥነ ልቡናና ከክብር ትሩፋትነት አልፎ ለኢኮኖሚ ጸጋነት እንዲተርፍ በደም ሳይሆን በላብ፤ በአጥንት ሳይሆን በጉልበት የምንከፍለው የመጪው ትውልድ ዕዳ እንዳለብን ዐድዋ ያስተምረናል፡፡
ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም ይላሉ ቀደምቶቻችን፡፡ የዐድዋ ድል ሀገራችንን የምናዘምንበትን ፍልስፍና የምናገኝበት፣ ሀገራችንን ወደ ከፍታ ለማድረስ የሚያስችለንን ዐቅም የምንሸምትበት፣ በየዘመናቱ እየመነዘርን እንደ ታዳሽ ኃይል የምንስፈነጠርበት ሕዝባዊ ዐቅም ነው፡፡ ዐድዋን ለኢትዮጵያውያን ምን ማለት እንደሆነ፣ እንኳን የድሉ ትሩፋት የደረሰን ኢትዮጵያውያን ቀርተን፣ ስንቅ ያጓጓዙት እንስሳት እንኳን ሳያውቁት አይቀሩም፡፡
ይህ የተጋድሎ ታሪካችን በዓለም ፊት ተገቢውን ቦታ እንዲይዝ፣ በነጻነት ፊት ብቻውን ተነጥሎ የቆመ አንድ የዛፍ ጭራሮ ሳይሆን በልምላሜ የተከበበ ጫካ እንዲሆን፣ በሳይንሳዊ ምርምርና በጥበባዊ ሥራችን ማረጋገጥና ማድመቅ ይኖርብናል፡፡ ነገረ ዐድዋን በጥበብ፣ በአካዳሚያዊ ፈለግ እና በማኅበረ ባሕላዊ ዐውድ መመርመር- ማክበር እና ማጥናት ያስፈልገናል፡፡
ይህ የሀገራችን ዕምቅ ሀብት የሆነ ታሪካዊ ድል ተገቢውን ክብር እንዲያገኝ ግጥሞችን የገጠሙ፣ ድርሳናትን የሰነዱ፣ ተውኔቶችን የደረሱ፣ ዜማዎችን የቀመሩ፣ መጣጥፎችን የከተቡ፣ የመድረክ ዝግጅቶችን ያቀናበሩ፣ የእግር ጉዞዎችን ያዘጋጁ፣ በሀገር ቤትና በውጭ የሚገኙ፣ ኢትዮጵያውያን፣ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ብዙ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ያለኝን ላቅ ያለ ክብርና ምስጋና በዚሁ አጋጣሚ አቀርባለሁ፡፡
ዐድዋ በውስን ፊልሞች፣ በጥቂት ድርሳናት፣ በጣት በሚቆጠሩ ዜማዎች፣ እፍኝ በማይሞሉ የታሪክ ምርምር ጽሑፎች፣ በእግር ጉዞ እና በመድረክ ትወና ብቻ ተዘርዝሮ እና ተዘከሮ የሚታለፍ አይደለም፤ በፍጹም፡፡
ያገባናል የምንል አካላት ሁሉ ከሥነ ጥበብ፣ ከእምነት፣ ከፍልስፍና፣ ከታሪክ፣ ከሴቶች ተሳትፎ፣ ከመሪነት ጥበብ፣ ከሀገራዊ አንድነት፣ ከውትድርና ሳይንስ፤ በኢኮኖሚ ራስን ከመቻል፤ ብሎም ከጥቁር ሕዝቦች የነጻነት እና የትግል ታሪክ ፋና ወጊነት ጋር በማስተሣሠር ዓለም ዓቀፋዊ ሥራ መሥራት ገና ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም ምሁራንና የጥበብ ሰዎች ዓለም አቀፋዊ ደረጃ ያለው ሥራ እንዲሠሩ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ መንግሥትም የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ያለውን ዝግጁነት ለማሳወቅ እወዳለሁ፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!"
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
አመሰግናለሁ፡፡
የካቲት 22 ቀን 2011 ዓ.ም