ቀጥታ፡

ሴቶች በአድዋ ጦርነት የነበራቸው ሚና በአግባቡ አልተነገረም- ምሁራን

አዲስ አበባ የካቲት 22/2011 ሴቶች በአድዋ ጦርነት ወቅት የነበራቸው ሚና በአግባቡ ያልተነገረና ታሪክ ሊዘክረው የሚገባ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ።

በአድዋ ጦርነት እቴጌ ጣይቱ ብጡልን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሴቶች በአዋጊነት ተሳትፈዋል፤ ጦር መርተው፣ መድፍ አስተኩሰው፣ ወታደር አዝዘው አዋግተዋል፤ ቀን ከውጊያ ማታ ከስንቅ ዝግጅት ሳይነጠሉም ረጅሙን የውጊያ ወራት አሳልፈዋል።

ይሁን እንጂ ይህ የሴቶች ሚና በታሪክ በተለይም ደግሞ በአድዋ ጦርነት ታሪክ እምብዛም አልተነገረም ይላሉ ምሁራን።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህር ዶክተር ሳሙኤል ነጋሽ ይህን የታሪክ ድክመት "በአድዋ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘርፎች ሴቶች በታሪክ ውስጥ የነበራቸውን ጉልህ ቦታ ታሪክ ሲዘክረው አይታይም" ሲሉ ይገልጹታል።

በሌሎች ጉዳዮች ሴቶች ላይ ተጽእኖ ሲደረግ እንደኖረው ሁሉ ታሪክም በሴቶች ላይ ተጽእኖ ሲያሳድር በመቆየቱ የሴቶችን ሚና አጉልቶ የማውጣቱ ነገር "እጅግም አይታይም” ነው ያሉት።

አብዛኛው የኢትዮጵያ ታሪክ ሁሉንም ነገሮች ያካተተ ቢሆንም ትኩረት ይሰጥ የነበረው “ለሃይማኖት፣ ለወታደራዊ ታሪኮች፣ ለጦር ገድሎችና ለፖለቲካ መሪዎች ታሪክ  እንደነበር በመጥቀስ።

በኢትዮጵያ በተለይም በአድዋ ጦርነት ሴቶች የነበራቸውን ሚና የሚያሳይ ስራ አለመሰራቱ ግን ስህተት መሆኑን መቀበል እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

ለአድዋ ጦርነት መንስኤ የነበረውን የጣልያኖች የተሳሳተ አካሄድና መሰሪነት ቀድመው የተረዱትና በባለቤታቸው በአፄ ምኒልክ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳደሩት እቴጌ ጣይቱ ብጡል ነበሩ።

እንደ እቴጌ ሁሉ የጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩት ሴቶች ስንቅ ከማዘጋጀትና የሞራል ቅስቀሳ ከማድረግ ባሻገር ለድል የሚበቃ ጠንካራ ብቃት ያለው ጦር በማብቃት ደረጃም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

“ሴቷ ባሏን፣ ወንድሟን እና አባቷን ለአገሩ በልበ-ሙሉነት እንዲቆም በማድረግ ረገድ የማይቆጠርና የማይለካ ሚና ተጫውታለች” ያሉት ዶክተር ሳሙኤል ይህ ባይሆን ኖሮ የአድዋ ታሪክ ሌላ ይሆን እንደነበር እምነታቸውን ገልጸዋል።

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ዶክተር አልማው ክፍሌም ይህንኑ ሃሳብ ይጋራሉ።

 “አማካሪዎቻቸው የአብዛኞቹ ሚስቶቻቸው ናቸው፤ ፊታውራሪዎች ነበሩ ሴቶች ደጃዝማች ሴቶች ነበሩ፣ የጦር መሪዎች ነበሩ፣ እነሱ አንደኛ ጦርነቱን እቴጌ በሚመሩበት ጊዜ ከእቴጌይቱ ጋር ብዙ ሴቶች ነበሩ፤ በአካል የተሳተፉ እንዳሉ አሁን ጥናት ያስፈልጋል እንጂ ስማቸውን ይዞ ሁሉ ማውጣት ይቻላል”

የታሪክ ተጽዕኖው የቀጠለ ቢሆንም ሴቶች ወደ አመራርነት የመምጣታቸውና ጉልህ ሚና የመጫወት ድርሻቸው እያደገ መምጣቱን የጠቀሱት ዶክተር ሳሙኤል ያም ሆኖ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

የዶክተር አብይ አህመድን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት መምጣት ተከትሎ የተጀመረው ሴቶችን የማብቃትና ወደ ከፍተኛ አመራርነት የማምጣት አስተሳሰብ ለአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጎነት የሚበጅ በመሆኑ ‘ሊቀጥል ይገባል” ሲሉም አክለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ወራሪውን የኢጣልያ ሰራዊት ድል በማድረግ የመለሱትና የጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነውን የአድዋ ድል ያስመዘገቡት የዛሬ 123 ዓመት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም