በዳባት ከተማ እስረኛ ያስመለጡ የፖሊስ አባላት ተያዙ - ኢዜአ አማርኛ
በዳባት ከተማ እስረኛ ያስመለጡ የፖሊስ አባላት ተያዙ
ጎንደር የካቲት 22/2011 በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ከተማ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ እስረኞች እንዲያመልጡ ያደረጉ አራት የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
በዞኑ ፖሊስ የማህበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል የሥራ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር በሬ ተሻገር ለኢዜአ እንዳሉት የእለት ተረኛ የሆኑ አራት የፖሊስ አባላት ኃላፊነታቸውን ባለመወጣት ክስ ተመስርቶባቸው በህግ ጥላ ስር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡
የፖሊስ አባላቱ በጥበቃ ወቅት ባሳዩት ቸልተኝነት በፖሊስ ጣቢያው በተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው የነበሩ 17 እስረኞች እንዲያመልጡ አድርገዋል፡፡
ዋና ኢንስፔክተር በሬ እንዳሉት ያመለጡት እስረኞቹ በነፍስ ግድያ፣ በህገ-ወጥ የጦር መሳሪያና በስርቆት ወንጀል ተጠርጠረው በፖሊስ ምርመራ ላይ የነበሩ ናቸው፡፡
እስረኞቹ የካቲት 19 ቀን 2011 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ላይ የታሰሩበትን ክፍል የእንጨት ግድግዳ በጀርባ በኩል ከስር ቆፍረው ማምለጣቸውንም አስታውሰዋል።
እንደ ኢንስፔክተሩ ማብራሪያ ፖሊስ ያመለጡትን እስረኞች በቁጥጥር ስር ለማዋል ከአካባቢው የፀጥታ ኃይል ጋር በመቀናጀት በከተማና በገጠር ጭምር የተጠናከረ አሰሳ እያካሄደ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣት በቁጥጥር ስር የዋሉትን የፖሊስ አባላት ህግ ፊት በማቅረብ ክስ መመስረት እንዲቻልም በአሁኑ ወቅት የምርመራ ሥራው መጀመሩን ዋና ኢንስፔክተሩ አስታውቀዋል፡፡