የህግ ጥሰቶችን በማስቆም በኩል የመንግስት ከልክ በላይ ትዕግስት ህብረተሰቡን ለስጋት መደረጉን ምሁራን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የህግ ጥሰቶችን በማስቆም በኩል የመንግስት ከልክ በላይ ትዕግስት ህብረተሰቡን ለስጋት መደረጉን ምሁራን ገለጹ
ደሴ የካቲት 22/62011 በሃገሪቱ ተለዋዋጭ በሆነ መንገድ የሚፈፀሙ የህግ ጥሰቶችን በማስቆም በኩል የመንግስት ከልክ በላይ ትዕግስት ህብረተሰቡን ለስጋት እንደዳረገው ምሁራን በጥናት ማረጋገጣቸውን ገለጹ፡፡
ሀገራዊ የሰላም ፣የዴሞክራሲና የልማት ኮንፈረንስ በሚል የተዘጋጀ ውይይት በወሎ ዩንቨርሲቲ ተካሄዷል፡፡
በውይይቱ "በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች፣ መልካም አጋጣሚዎችና ስጋቶች" የሚል ጥናታዊ ጹህፍ ያቀረቡት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ሰሚር የሱፍ እንዳሉት የመንግስት ከልክ በላይ ትዕግስት ህብረተሰቡን ለስጋት ዳርጎታል፡፡
በተለያዩ ክልሎች ሁከት ተከትሎም መፈናቀል፣ የህግ የበላይነት ጥሰትና ዝርፊያ ሲበራከት ቆራጥ እርምጃ ባለመወሰዱ ወንጀሎች መበራከታቸውንም ገልጸዋል፡፡
" ይህ ደግሞ ህብረተሰቡ በለውጥ ኃይሉ ላይ ያሳደረው እምነት እንዲሸረሽርና ስጋት እንዲገባው አድርጎታል "ብለዋል፡፡
በጥናታቸውም ወጥነት የሌለው ያልተረጋጋ ፖለቲካ ፣ አንድ ከሚያደርጉ ጉዳዮች ይልቅ በልዩነቶች ላይ ማተኮር ፣ ከጋራ ዓላማ ይልቅ የግል ጥቅምን ማስቀደም፣ ብሄር ክፍፍልና የሀብት ብክነት የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ እንዳይቀጥል ከፍተኛ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡
"የታዩ ለውጦች በግጭት ሳይሆን በማህበራዊ ንቅናቄ መምጣታቸውና ለውጥ አራማጅ አመራር መኖሩ ደግሞ መልካም እድሎች ነበሩ " ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡ ካደረበት ስጋትና ኢትዮጵያን ከመበታትን አደጋ ለመታደግ መንግስት በየክልሉ በብሄር ፖለቲካ ብቻ የተጠመዱ አመራሮችን ማስተካከል እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡
ወጣቱም ከዚህ በፊት የተፈጸሙ ውስብስብ ችግሮች በአንድ ጀንበር እንዲፈቱ መፈለጉ ተገቢነት ስላሌለው በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ምክንያታዊ መሆን ይኖርበታል፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ምክትል ዲን አቶ ሰብስቤ አዲሴ በበኩላቸው "የለውጡ ጥያቄዎችና የሽግግር ተስፋ፣ ስኬትና ስጋት" የሚል ጥናታዊ ጹህፍ አቅርበዋል፡፡
ለዉጡ እንዲመጣ ግፊት ያደረጉ ወጣቶች ችሎታቸውን ያማከል ቦታ አለመያዛቸውና ከታች እስከ ላይ ቅሬታ የፈጠሩ አመራሮችን ከማንሳት ይልቅ ቦታ ለውጥ መደረጉን እንደ ስጋት አንስተዋል፡፡
"መንግስት በተግባር ላይ የሚውል ምክክር በየደረጃው በማድረግ የህዝቡን ስሜታ ማዳመጥና ለውጡን ማስቀጠል ይጠበቅበታል" ብለዋል፡፡
ምሁሩ እንዳሉት በከፍተኛ አመራሮች የሚስተዋለውን ውስጣዊ ችግር በመፍታት አጋርና እህት ድርጅቶች ጋርም መተማመንን መፍጠር ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
" ወጣቱ በየአካባቢው ቢደራጅ አገር አያፈርስም " ያሉት አቶ ሰብስቤ ከሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች ወንድም እህቶች ጋር ተደጋግፎ አንድነቱን በማስጠበቅ ኢትዮጵያን ያለ ስጋት ማስቀጠል እንደሚገባ መክረዋል፡፡
ከስሜት ተላቆ ለዴሞክራሲና የህግ የበላይነት መከበር የድርሻውን እንዲወጣም ጠቁመዋል፡፡
ወሎ ዩንቨርሲቲ በተደጋጋሚ የሚያካሂዳቸው ኮንፈረንሶች በሰላምና አንድነት ግንባታ ተጨባጭ ለውጥ እያሳየ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ጹህፍና የግጭት አወጋገድ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ገብረየሱስ ተክሉ ናቸው፡፡
" ሁላችንም የአባቶቻችን አንድነትና የመቻቻል እሴት ከታሪክ ተረድተን ኢትዮጵያን ከጥፋት ለመታደግ መስራት ይጠበቅብናል" ብለዋል፡፡
በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች ትውልዱን በጥሩ ስነ ምግባር በማነጽ የተጀመረው ለውጥ እንዳይቀለበስ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡
" የየክልል አመራሮች ከጠባብ የኔነት ስሜት ተላቀውና አስተሳሰባቸውን በክልል ሳያጥሩ አንድ ኢትዮጵያን ማስብ ግድ ይላቸዋልም "ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ህዝባዊ የምክክር መድረክ ፕሬዝዳንት ኢንጅነር ጌታሁን ሁሴን በበኩላቸው ልማትና ዴሞክራሲ ጎልብቶ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን በቅንጅት ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠርም በተለያዩ ክልሎችና ዩኒቨርሲቲዎች ግንዛቤ ለመፍጠር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ትውልዱ አኩሪ ታሪኩን ጠብቆ ሀገሩን ከድህነት ለማውጣት የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
" የቀረቡ ጥናታዊ ጽሁፎች በለውጡ አንድነትና ሰላም ላይ ያተኮሩ፣ ችግሮችን ከነመፍትሄያቸው ያሳዩ በመሆናቸው ከመደርደሪያ ወጥተው ተግባር ላይ እንዲውሉ የድርሻችን እንወጣለን" ብለዋል፡፡
ዘንድሮ የተካሄዱት ጥናቶቹ ችግሩ በነበረባቸው የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለናሙናነት ተመርጦ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ለሁለት ቀናት በተካሄደውና ትናንት ማምሻውን በተጠናቀቀው ውይይቱ አስር ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተወጣጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራንና የመንግስት አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡