ቀጥታ፡

በሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈፀም የህግ ታራሚዎች ገለፁ

አዲስ አበባ የካቲት 22/2011 በሸዋሮቢት ተሃድሶ ልማት ማዕከል ማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈፀም የህግ ታራሚዎች ገለፁ።

ከዚህ በፊት በመጥፎ ተግባራቸው የተገመገሙ የማረሚያ ቤቱ የአመራርና የጥበቃ አባላት በታራሚው ላይ የበቀል እርምጃ እየወሰዱ ነው ሲሉም ነው ታራሚዎቹ የተናገሩት።

"ገምግመን በወንጀል ሊጠየቁ የሚገባቸው አመራሮች አሳልፈን ሰጥተን ምንም የተደረገ ነገር የለም"

ወጣት ጌታቸው አሰፋ

የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር በበኩሉ ታራሚዎቹ ከጥበቃ አካላት ጋር በሚፈጥሩት ያልተገባ እሰጥአገባ አልፎ አልፎ ከሚፈጠር ግጭት ያለፈ ይህ ነው የሚባል የሰብዓዊ መብት ጥሰት የለም ይላል።

የሸዋሮቢት ተሃድሶ ልማት ማዕከል ማረሚያ ቤት የህግ ታራሚዎችን በተለያዩ ሙያ በማሰልጠን ከህበረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ በማድረግ ይታወቃል።

በተያዘው ዓመት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንኳ ከ370 በላይ የህግ ታራሚዎችን በማሰልጠን የሙያ ብቃት ምዘና እንዲወስዱ አድርጓል።

ታራሚዎቹ ከሰለጠኑባቸው ዘርፎች መካከል  እንጨትና ብረታ ብረት፣ ሽመና፣  የጸጉርና የውበት፣ የቅርጻ ቅርፅና የቧንቧ ስራዎች ይገኙበታል።

ስልጠናው ህይወታቸውን ለማሻሻል የሚያግዛቸው መሆኑን ከህግ ታራሚዎች አንደበት ሰምተናል።

በሌላ በኩል ግን ግርፋትን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጸምባቸው የህግ ታራሚዎች እንዳሉ ነው ታራሚዎቹ በስፍራው ለተገኘው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር የገለፁት።

በማረሚያ ቤቱ የሚገኙ የህግ ታራሚዎች እንዳሉት፤ በማረሚያ ቤቱ በፊት አሰቃቂ ድርጊት በመፈጸም የገመገምናቸው የአመራርና የጥበቃ አባላት ዛሬም ቦታው ላይ በመሆናቸው የበቀል እርምጃ እየወሰዱ ነው።

ወጣት ጌታቸው አሰፋ እንዳለው”በቃለ መጠይቅ  የታራሚውን ችግር ስለ ፍትህ ስለሰብዓዊ መብት ጉዳይ ተናግረን ነበር፤ ለመንግስት እንዲቀርብልን ተናግረናል፤ ነገር ግን የታየ ለውጥ የለም ፤ የባሰ ፍትህ ነው ያጣነው ሰብዓዊ መብት ጥሰቱም እየባሰበት ነው፤ ምክንያቱም ገምግመን በወንጀል ሊጠየቁ የሚገባቸው አመራሮች አሳልፈን ሰጥተን ምንም የተደረገ ነገር የለም ተመልሰው እነሱ ናቸው ያሉት አልተነሱም።"ብሏል፡፡

ወጣት ዮናስ ወንድሙ በበኩሉ "ዞን 5 የሚባል ጨለማ ቤት መጥቷል እኛ የምናውቀው 4 ዞን ነው ከዚግቢ ስመጣ ከሃምሌ ወር በኋላ ዞን 5 ተብሎ ከዚያ ተገልለው የሚኖሩ ልጆች አሉ፤ ይሄንን ስላወራሁ ነገ እኔም ልገባ እችላለሁ፤ አሁን እንደዚህ የምናገረው እየፈራሁ ነው፤ ለምን እዛ መግባት አልፈልግም ያለምንም ጥፋት ነው እየገባን ያለነው።"

የሸዋሮቢት ተሃድሶ ልማት ማዕከል ማረሚያ ቤት ዋና አስተዳዳሪ ኮማንደር እንደሻው ማሙዬ በበኩላቸው የህግ ታራሚዎች ከጥበቃ አባላት ጋር በሚፈጥሩት አለመግባባት መጠነኛ ግጭት ሊከሰት ይችላል ነው የሚሉት።

"ሀሳባቸውን ለመገናኛ ብዙሃን በመግለጻቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸምባቸው የሚደረግበት ምንም ዓይነት ሁኔታ የለም "

የሸዋሮቢት ተሃድሶ ልማት ማዕከል ማረሚያ ቤት ዋና አስተዳዳሪ ኮማንደር እንደሻው ማሙዬ

ኮማንደር እንደሻው እንዳሉት በታራሚዎች መካከል ግጭት ይፈጠራል፤ የጥበቃ አባላቱም ግጭቱን ለመቆጣጠር ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት በታራሚው ጥቃት ይሰነዘርባቸዋል።  

"ሌሊት ድብደባ አለ በሚለው በጥቅሉ አልስማማም ግን አልፎ አልፎ ግጭቶች ሲነሱ ግጭቶችን ለማብረድ አባል ገብቶ ስነ ስርዓት በሚያስይዝበት ጊዜ ተመልሰው አባሉ ላይ ድንጋይ በመወርወር በርካታ አባሎቻችን በድንጋይ የተመቱበት ሁኔታ አለ፤ ያን ስርዓት ለማስያዝ የሚወሰድ ነገር ሊኖር ይችላል ወይም ለማምለጥ የሚሞክር ታራሚ እንዳያመልጥ ለማድረግ የሚደረግ ስራ ይኖራል፤ ከዛ ባለፈ ድብደባ አለ ለማለት ይከብዳል።"

"ሀሳባቸውን ለመገናኛ ብዙሃን በመግለፃቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸምባቸው የሚደረግበት ምንም አይነት ሁኔታ የለም፤ እነሱ የመሰላቸውን የፈለጉትን መናገር ይችላሉ" ሲሉም ኮማንደሩ ተናግረዋል። 

በተቋሙ አገልግሎት ሰጭዎች ሰብዓዊ ክብራችንን ከመንካት ወጭ በአግባቡ አያስተናግዱንም የተከለከሉ ነገሮች በድብቅ በጥበቃ አካላት ወደማረሚያ ቤቱ እየገባ ሳለ ያስገባውን አካል በዝምታ በማለፍ እኛ ላይ ግን በደል እያደረሱብን ነው ይላሉ ታራሚዎቹ።

ወጣት ምህረትአብ ካሳዬ እንዳለው " ዶክተርን የሚያክል ነገር ይመታሃል፤ ይማታሉ እኔ ዶክተር ማለት ሰው ሲያክም ነው የማውቀው ወይስ ከፍለን ስንታከም ብቻ ነው ሊንከባከቡን የሚገባው "ብሏል፡፡

 “ሲጋራ ክልክል ነው በተቋም ደረጃ ግን ሲጋራ የሚያስገቡት ራሳቸው ናቸው፤ አንድ ሲጋራ 25 ብር ነው የሚሸጠው።" ያሉት ደግሞ አቶ ዘሚካኤል ናቸው፡፡

የማረሚያ ቤቱ ዋና አስተዳዳሪ ኮማንደር እንደሻው ማሙዬ አብዛኞቹ ታራሚዎች የአዲስ አበባ ልጆች በመሆናቸው በሪፈር ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ከሀኪሞች ጋር አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ ይገባሉ፤ የሚሰጣቸውን መድሃኒትም በአግባቡ አይወስዱም ብለዋል።

"ታራሚዎች በህክምና ዙሪያ ብዙም አይረኩም የማይረኩበት ምክንያት ምንድን ነው አብዛኛው 99 በመቶ ታራሚያችን የአዲስ አበባ ታራሚ ስለሆነ ሸዋሮቢት መቆየት አይፈልጉም በሪፈርም በዝውውርም አዲስ አበባ መመለስ ይፈልጋሉ፤ ስለዚህ ያችን ሪፈር ካላገኘ ደስተኛ ያለመሆንና ሃኪሙ የሚያዝለትን መድሃኒቶችን ያለመቀበል ነገር አለ።"

የህግ ታራሚዎች እነሱ የሚፈልጉትን እንጂ ሃኪሙ የሚያዝላቸውን መድሃኒት መጠቀም አይፈልጉም፤ ከሃኪም ትዕዛዝ ውጭ መድሃኒት ካልተሰጠን ለሚሉት ታራሚዎች ልናደርግ የምንችለው ነገር የለም ብለዋል።

"በተቋሙ ሲጋራ ማጨስ ክልክል ቢሆንም አንዳንድ ስነ ምግባር የጉደላቸው የፖሊስ አባላት በድብቅ ይዘው ሲገቡ አግኝተናቸዋል፤ እነርሱ ላይም አስተዳደራዊ እርምጃ ወስደናል" ብለዋል ኮማንደር እንደሻው።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም