ቀጥታ፡

የሞያሌ አካባቢን የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ ኢትዮጵያና ኬንያ በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ

አዲስ የካቲት 22/2011 ኢትዮጵያና ኬንያ የሚዋሰኑበትን የሞያሌ ድንበር አካባቢ የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ በጋራ እንዲሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ፡፡

የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በበኩላቸው አገሮቹ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር ያላቸውን ምቹ ሁኔታ አሟጦ መጠቀም እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

መሪዎቹ ይህንን ያሉት የኢትዮጵያ የኬንያ ኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው ፎረም ላይ ነው፡፡

ፎረሙ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከሁለቱ አገሮች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በተጨማሪ 100 የሚሆኑ የኬንያ ባለሀብቶች እየተሳተፉበት ይገኛሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ በዚሁ ወቅት ''ኢትዮጵያና ኬንያ በጋራ ከሰሩ የሚሳናቸው እንደሌለ የማራቶን አትሌቶቻችን ምስክሮች ናቸው'' ብለዋል፡፡

አገሮቹ ያላቸውን የቆየ ግንኙነት ወደጋራ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መቀየር እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ አገሮች በመሠረተ ልማት በመተሳሰር የሞያሌ አካባቢ የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማዕከል ማድረግ እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለዚህም መንግሥታቸው የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በበኩላቸው በጋራ ለመልማት ካላቸው እድል አንፃር የሄዱት ርቀት የሚጠበቅባቸውን ያህል አለመሆኑን አውስተዋል፡፡

''በመሆኑም ያሉትን ምቹ ሁኔታ አሟጠን በመጠቀም የዜጎቻችንን ኑሮ ማሻሻል አለብን'' ብለዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ሞያሌ የተዘረጋው የፍጥነት መንገድም ትስስሩን ለማሳለጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ በኬንያ በነበራቸው የስራ ጉብኝት የሁለትዮሽ ትብብርን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከኬንያው ፕሬዚዳንት ጋር ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያና ኬንያ ፖለቲካዊና ምጣኔ ኃብታዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የአገሮቹን እድገትና ብልፅግና ሊያፋጥኑ በሚያስችሉ የትብብር መስኮች ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል።

ከአይሲዮሎ - ሞያሌ - አዲስ አበባ የሚዘልቅ መንገድ እንዲሁም ከናይሮቢ አዲስ አበባ የሚደርስ የባቡር ትራንስፖርት ለመዘርጋት መስማማታቸውም እንዲሁ።

የኬንያ መንግስት ኢትዮጵያ በላሙ ወደብ መሬት የምታገኝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ቃል የገባ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግስትም በበኩሉ በሚያገኘው መሬት ላይ የሎጂስቲክ እንቅስቃሴ መገልገያዎችን የሚያለማ መሆኑን አረጋግጧል።   

በወቅቱም ሁለቱ አገሮች የሚዋሰኑባትን ሞያሌ "የጋራ ከተማና የኢኮኖሚ እንብርት" ለማደረግ የሚያስችል ፕሮጀክት ለመንደፍ መስማማታቸውም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም