ቀጥታ፡

መሪዎቹ የሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክን ሊጎበኙ ነው

ሀዋሳ የካቲት 22/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ዛሬ የሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክን ይጎበኛሉ።

የሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ከተማ እንዳሉት ጉብኝቱ የሚካሄደው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር በማሰብ ነው።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተመሳሳይ በኬኒያ ተገኝተው ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

በዚህም መሪዎቹ በሁለቱ ሀገራት መካከል የንግድ ትስስራቸውን በተለይ በሀገራቱ አየር መንገዶች መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸው ይታወሳል።

ከጉብኝቱ በተጨማሪ መሪዎቹ ባደረጉት ውይይት በኬኒያ ታስረው የነበሩ ኢትዮጵያውያን እንዲፈቱ መደረጉ ይታወሳል።

ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየውና በሌሎች የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም