ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ
ጎንደር የካቲት21/2011 በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከቄያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም በተጀመረው የገቢ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ።
በሁለቱ ዞኖች ቤታቸው በቃጠሎ ለወደመባቸው ወገኖች ቤት ገንብቶ ለማቋቋም ከ77 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ እንደሚያስፈልግም ተመልክቷል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የኢኮኖሚ አማካሪና የተፈናቃዮች የእለት እርዳታና መልሶ ማቋቋም ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ አየነው በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት በሁለቱ ዞኖች የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ55ሺህ በላይ ደርሷል፡፡
በክልሉ መንግስት የተቋቋመው ግብረ ኃይል ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችል ዕቅድ ነድፎ ወደ ሥራ መግባቱንም ተናግረዋል።
ግብረ ኃይሉ እስካሁን ባደረገው እንቅስቃሴ ከንግዱ ማህበረሰብ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከፋይናንስ ተቋማትና ከክልሉ ህብረተሰብ ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዝብ ማሰባሰቡንም ገልጸዋል፡፡
የገንዘብ ድጋፉን በዋናነት ካደረጉት መካከልም የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም 25 ሚሊዮን ብር፣ ጥረት ኮርፖሬት 10 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የአማራ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (አዴፓ) 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
አቶ አየነው እንዳሉት በሁለቱ ዞኖች በግጭቱ መኖሪያ ቤታቸው ተቃጥሎ ለወደመባቸው አባውራዎች ቤት ገንብቶ ለማስረከብ እንዲቻል 77 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ በጥናት ተለይቷል፡፡
ተፈናቃዮችን ከእለት እርዳታ በዘለለ ዘላቂ በሆነ መንገድ ማቋቋም እንዲቻል ግብር ኃይሉ የጀመረውን ጥረት በማገዝ በኩል የክልሉ ህዝብና ባለሀብቶች ድጋፋቸውን አጠናከረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጸሐይ ቀለም ፋብሪካ ባለቤት አቶ ሕብረት ሽታሁን ግምቱ 176ሺህ ብር የሚያወጣ 90 ኩንታል አንደኛ ደረጃ ፍርኖ ዱቄት ለተፈናቃዮች እንዲሰጥ ለማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዛሬ አስረክበዋል፡፡
በወረታ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ 200 መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ባዋጡት 47ሺህ ብር የገዙትን 60 ኩንታል በቆሎ፣ 600 ዳቦና ሁለት ጆንያ አልባሳት በመጠለያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች አስረክበዋል፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ጣምያለው እርዳታውን ከተረከቡ በኋላ እንደተናገሩት ለወገን ደራሽ ወገን ነው በሚል ህብረተሰቡና ባለሀብቶች ለተፈናቃዮች ያደረጉት ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በክልሉ መንግስትና በየደረጃው ባሉ አካላት የተጀመረውን ጥረት ለማሳካትም ህብረተሰቡ ከእለት እርዳታ ባሻገር በገንዘብ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም አመለክተዋል፡፡